ሁዋዌይ ያስተዋወቀው የመጀመሪያው 3 ቦታ የሚታጠፍ ስልክ ምን የተለየ ነገር ይዟል?
የቻይናው ሁዋዌይ 10.2 ኢንች ስክሪን ስፋት ያለው 3 ቦታ የሚታጠፍ ስማርት ስልክ ይፋ አድርጓል
ስማርት ስልኩ በ2 ሺህ 800 ዶላር ወይም ከ300 ሺህ ብር በላይ ዋጋ የተቆረጠለት ሲሆን፤ ይህም አነጋጋሪ ሆኗል
የቻይናው ሁዋዌይ ኩባንያ በአይነቱ ለየት ያለ እና ሶስት ቦታ የሚተጣጠፍ አዲስ ስማርት ስልክ ባሳለፍነው ሳምንት ይፋ አድርጓል።
አሁን ላይ ሁለት ቦታ የሚታጠፉ ስማርት ስልኮች እየተለመዱ የመጡ ሲሆን፤ ሁዋዌይ ይፋ ያደረገው ሶስት ቦታ ተጣጣፊ ስማርት ስልክ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።
አዲሱ የሁዋዌይ ሜት (Mate XT) የሚል ስያሜ ያለው ስማርት ስልኩ 3 ቦታ የሚተጣጠፍ ሲሆን፤ 10.2 ኢንች የስክሪን ስፋት አለው።
ሁዋዌይ ሜት (Mate XT) ከስልክነት በዘለለ እንደ ላፕቶፕ በመሆን መደበኛ የሆኑ ስራዎችን መከወን እንደሚያስችልም ኩባንያው አስታውቋል።
በዚህም ሶስት ቦታ የታጠፈውን ስክሪን ሙሉ በሙሉ በመዘርጋት ድረ ገጾችን ለመከፈት እና ለማንበብ እንዲሁም የጥናት ስራዎችን ለማከናወን ያስችላል ተብሏል።
በተጨማሪም የስማርት ስልኩ ግዙፍ ስክሪን ኢሜል ለመላላክ፣ የፋይናንስ አስተዳደሮ ተግባራትን ለማከናወን እንዲሁም ቪዲዮዎችን ለማጫወት የሚስችል ነው።
ሶስት ሌንሶች ያሉትና ከፍተኛ የካሜራ ጥራት አለው የተባለው ስማርት ስልኩ፤ 50 ሜጋ ፒክስል የምስል ጥራት ማንሳት የሚችል እንደሆነም ተነግሯል።
አዲሱ የሁዋዌይ ሜት (Mate XT) ምን ይዟል?
የሁዋዌይ ሜት (Mate XT) ስማርት ስልክ ሁለት ናኖ ሲም ካርዶችን የሚቀበል ሲሆን፤ GSM / CDMA / HSPA / CDMA2000 / LTE / 5G ኔትዎርት የሚያስተናግድ ቴክኖሎጂ አለው።
ሃርሞኒ (HarmonyOS 4.2) የተባለ እና በቻይና የተሰራ ኦፕሬቲንግ ሲስተም የሚጠቀም መሆኑንም ሁዋዌይ ኩባያ አስታውቋል።
የመረጃ ማከማቻ ወይም ሜሞሪውን ስንመለከትም፤ ከ1 ቴራ ባይት ጀምሮ በሶስት አይነት የቀረበ መሆኑ ተነግሯል።
በዚህም መሰረት 256 ጊጋ ባይት (GB) በ16 ጊጋ ባይት GB RAM፣ 512 ጊጋ ባይት (GB) በ16 ጊጋ ባይት (GB) RAM እንዲሁም 1 ቴራ ባይት (TB) 16 ጊጋ ባይት (GB) RAM ነው የቀረቡት ተብሏል።
በካሜራም ከፍተኛ ጥራት አለው የተባለ ሲሆን፤ እስከ 50 ሜጋ ፒክስል የምስል ጥራት ማንሳት የሚችል ካሜራ ተገጥሞለታል።
በስልኩ ጀርባ ላይ የተገጠሙ ሶስት የካሜራ ሌንሶችም፤ የመጀመሪያ ካሜራ 50 ሜጋ ፒክስል ሲሆን፤ እያንዳንዳቸው 12 ሜጋ ፒከስል የሆኑ ሁለቱ ሌንሶች ደግሞ የቴሌፎቶ እና ርቀትላይ የሚገኝ ነገርን ማንሳት የሚያስችሉ ናቸው።
8 ሜጋ ፒክስል የፊትለፉት (ሰልፊ) ካሜራም የተገጠመለት ሲሆን፤ 5600 mAh ባትሪም ተገጥሞለታል።
በቀይ እና በጥቁር ቀለም ለገበያ ይቀርባል የተባለው ስማርት ስልኩ ከአራት ቀናት በኋላ ማለትም መስከረም 10 ቀን ለገበያ እንደሚቀርብ ይጠበቃል።
ለስማርት ስልኩ የተቆረጠው የመሸጫ ዋጋ 2 ሺህ 800 የአሜሪካ ዶላር ወይም ከ300 ሺህ ብር በላይ ሲሆን፤ ዋጋው እጅግ እያነጋገረ ነው።