“ወደ ትግራይ እየተላከ ካለው ድጋፍ 70 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ ነው” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴ የተባበሩት መንግስታትን አመስግኗል
ዛሬ ጠዋት ለተመድ የተለያዩ ኤጄንሲዎች በትግራይ ክልል ሁኔታ ላይ ማብራሪያ መሰጠቱ ተገለጿል
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ኢትዮጵያ ከሰሞኑ ባካሄደችው የውጭ ግንኙነት ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫቸውም ኢትዮጵያ የሕግ ማስከበር ስራውን እያጠናቀቀች መሆኑንና የፖሊስ ስራዎች ብቻ እንደሚቀሩ ገልጸዋል፡፡ ይህንንም “ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲረዳ አድርገናል” ብለዋል፡፡
“የኤርትራ ወታደሮች በተለያዩ የትግራይ ክልል ከተሞች ገብተው እየዘረፉ ነው” ስለመባሉ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ የኤርትራ ወታደሮች በዘረፋ እንዳልተሰማሩ ገልጸዋል፡፡ “የኤርትራ ወታደሮች የደንብ ልብስ ተሰፍቶ እየታደለ” መሆኑን ገልጸው ይህም “ኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ገብታለች” ለማስባል ታቅዶ የተደረገ ነው ብለዋል፡፡
አሁን ላይ የፌዴራል መንግስት ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በመነጋገር እየሠራ ነው ያሉት አምባሳደር ዲና የሰብዓዊ እርዳታ ቁሳቁስ እየተላከ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
ለሰብዓዊ እርዳታ በሚል ሌሎች አጀንዳዎችን ይዘው ወደ ስፍራው የሚሄዱ እንዳሉ የገለጹት ቃል አቀባዩ ፣ “በቀጣናው ሰላም እንዲመጣ የሚፈልጉ እንዳሉ ሁሉ የአካባቢውን ሰላም መሆን የማይፈልጉም አሉ” ብለዋል፡፡
በሱዳን ስደት ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ዲና ወደ ትግራይ እየተላከ ካለው ድጋፍ ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ መንግስት በራሱ አቅም የሚያቀርበው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዛሬ ጠዋት ላይ የተባበሩት መንግስታት የተለያዩ ኤጄንሲዎች ኃላፊዎች በወቅታዊ የትግራይ ክልል ሁኔታ ላይ ማብራሪያ እንደተሰጣቸውም ነው የጠቆሙት፡፡
የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የኤርትራ ወታደሮች ወደኢትዮጵያ መግባታቸውን የሚያሳይ ማስረጃ እንደሌለ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
አምባሳደር ዲና የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ኢትዮጵያን በተመለከተ እየሰጡ ላሉት ገንቢ አስተያየት ምስጋና እናቀርባለን ብለዋል፡፡ ለኢትዮጵያ መረጋጋት የተባበሩት መንግስታት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጹንም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ጉብኝት
የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ታህሣሥ 4 ቀን 2013 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት መምጣታቸው ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሁለት ቀናት እንደሚቆዩ ተነግሮ የነበረ ቢሆንም በመጡበት ዕለት ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው በብዙዎች ዘንድ መነጋሪያ ሆኖ ቆይቷል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የተሳካ እንደነበር ግን የሱዳን ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ይህንን በተመለከተ መግለጫ የሰጠው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትም በተመሳሳይ የአብደላ ሃምዶክና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ውይይት የተሳካ እንደነበር ገልጿል፡፡ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) በዋና መስሪያ ቤቱ ጅቡቲ በሚያደርገው ስብሰባም በትግራይ ክልል ጉዳይ ውይይት እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡