በአንድ ወቅት ከኦባማ ጋር የደነሱት አዛውንት ሴት በ113 አመታቸው አረፉ
ማክላውሪን፤ ኦባማን ባገኙበት ወቅት “ጥቁር ፕሬዝዳንት በማየቴ እጅግ ደስተኛ ነኝ” ያሉበት አጋጣሚ አይዘነጋም
ባራክ ኦባማ በቨርጂኒያ ማክላውሪን ሞት ተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል
እንደፈረንጆቹ በ2016 በዋይት ሀውስ ከቀድሞው አሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ እና ከቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማ ጋር በደስታ የደነሱት ቨርጂኒያ ማክላውሪን በ113 አመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡
ልጃቸው ፌሊፔ ካርዶሶ ጁኒየር ማክሰኞ እንደተናገሩት ከሆነ ማክላውሪን ያረፉት ሰኞ ማለዳ በኦልኒ ሜሪላንድ በሚገኘው በታቸው ነው፡፡
የማክላውሪን ህልፈት ተከትሎ የተሰማቸውን ሀዘን በትዊተር ያሰፈሩት ባራክ ሁሴን ኦባማ “ቨርጂኒያ በሰላም እረፊ” ሲሉ ጽፈዋል፡፡
ኦባማ በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያው ጥቁር መሪ ሆነው ወደ ስልጣን በመጡበት ወቅት ቨርጂኒያ ማክላውሪን በዋይት ሃውስ ተገኝተው በ106 አመታቸው ደስታቸው የገለጹበት ቪዲዮም ሃዘናቸው ከገለጹበት ፖስት ጋር አጋርተዋል፡፡
ቨርጂኒያ ማክላውሪን በወቅቱ ኦባማን " የምነግርህ ነገር ቢኖር፤ በጣም ደስተኛ ነኝ" ብሏቸው ነበር፡፡
"ጥቁር ፕሬዝዳንት ፤ እንዲሁም ጥቁር ቀዳማዊት እመቤት፤ ደስ ይላል! " ሲሉም ነበር በወቅቱ ስሜታቸውን የገለጹት፡፡
በተጨማሪም ማክላውሪን "ከፕሬዝዳንት ጋር ተገናኝቼ አላውቅም ፤ በህይወቴ ጥቁር ፕሬዝዳንት አያለሁ ብየም አስቤ አላውቅም" ያሉበት አጋጣሚም አይረሳም፡፡
ቨርጂንያ ማክላውሪን የተወለዱት ህይወት ለአሜሪካውያን ከባድ በነበረበት እንደፈረንጆቹ በ1909 ነው፡፡
ወቅቱ በተለይም እንደ ቨርጂንያ ማክላውሪን ለመሳሰሉ አፈሮ-አሜሪካን መብታቸው ለመጠየቅ የሚቸገሩበት እንደነበርም ይነገራል፡፡
እናም በእድሜያቸው ለጥቁሮች መብት ሲል መስዋእትነት ከፈለውን ማርቲን ሉተር ኪንግ ሞት በእውን ለተመለከቱ ማክላውሪን የኦባማ መምጣት ትልቅ ትርጉም እንደነበረው ይነገራል፡፡
ኣዛውንቷ ሴት ቨርጂንያ ማክላውሪን ዋይት ሃውስ ድረስ ተገኝተው ደስታቸውን የገለጹት አጋጣሚ ምክንያትም ይህ እንደነበር ይገለጻል፡፡