ባራክ ኦባማ፤ የበለጸጉ ሀገራት የአየር ንብረት ቀውስን የመቋቋሙን ኃላፊነት በቀዳሚነት እንዲወስዱ ጥሪ አቀረቡ
ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ባሳሰቡበት ንግግራቸው የበለጸጉ ሀገራት "ሸክሙን" በቀዳሚነት ይውሰዱ ብለዋል
ኦባማ 2ኛ ሳምንቱን በያዘው የግላስኮው የዓለም የአየር ንብረት ጉባዔ ንግግር አድርገዋል
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የበለጸጉ ሀገራት የአየር ንብረት ቀውስን የመቋቋሙን ኃላፊነት በቀዳሚነት እንዲወስዱ ጥሪ አቀረቡ፡፡
ኦባማ 2ኛ ሳምንቱን በያዘውና በስኮትላንድ ግላስኮው በመካሄድ ላይ ባለው የዓለም የአየር ንብረት ጉባዔ ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡
ዓለም በዓመታት ሊቀለበስ ከማይችል የአየር ንብረት አደጋ ውስጥ መውደቋን ቁንጮ የዓለማችን ሳይንቲስቶች አስታወቁ
በንግግራቸው ሁሉም የድርሻውን ሊወጣና መስዋዕትነት ሊከፍል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ሁላችንም ልንሰራው የሚገባ የቤት ስራ አለ ያሉት የቀድሞው ፕሬዝዳንት የአየር ንብረት ለውጡን ተከትሎ የሚመጡ ቀውሶችን የመቋቋሙን "ሸክም" የበለጸጉት ሀገራት በቀዳሚነት እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኦባማ የፓስፊክ ውቅያኖስ ደሴታማ ሃገራት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ስለተጋረጠባቸው ከባድ የህልውና ችግር በተመከረበት መድረክ ላይ ነው ንግግር ያደረጉት፡፡
በንግግራቸው የደሴት ሃገራቱ ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን በመጠቆም አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ኦባማ ራሳቸው ተወልደው ያደጉት በሃዋይ ደሴት ነው፡፡ ይህ መሆኑም ደሴታማ ሃገራት የተጋረጠባቸውን ችግር እንዳውቅ ረድቶኛል ብለዋል፡፡
የበለጸጉ ሀገራት ለአዳጊ ሃገራት ‘እንሰጣለን’ ያሉትን የ100 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ድጋፍ እንዲሰጡ ህብረቱ ጠየቀ
አሁን ቃል የተገባው ቢተገበር እንኳን የዓለምን አማካይ የሙቀት መጠን እንደታሰበው ከ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺዬስ በታች ማድረግ አንችልም ያሉት የቀድሞው ፕሬዝዳንት የተግባር ስራዎች እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል፡፡
የ2015ቱ የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ሲፈረም የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ነበሩ፡፡ በወቅቱ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችሉ ጠንካራ እርምጃዎችን ለመውሰድ ቃል ገብተው ነበር፡፡
ሆኖም ተክተዋቸው ስልጣን የያዙት ዶናልድ ትራምፕ እርምጃዎችን ቃል በተገባው መሰረት መውሰድ አይደለም አሜሪካ ከስምምነቱ እንድትወጣ አድርገዋል፡፡
በኦባማ የአስተዳደር ዘመን የውጭ ጉዳይ የነበሩትን ጆን ኬሪን የአየር ንብረት ልዩ መልዕክተኛ አድርጎ የሾመው የጆ ባይደን አስተዳደር ግን ወደ ዓለም አቀፉ ስምምነት መመለሱን አስታውቋል፡፡
ፕሬዝዳንት ባይደን ራሳቸው ባሳለፍነው ሳምንት በጉባዔ መክፈቻ ላይ ተገኝተው እንደነበር ይታወሳል፡፡