“ትራምፕ ለኮሮና የሰጡት ምላሽ ምስቅልቅሉ የወጣ ነው” ሲሉ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ኦባማ ገለጹ
“ትራምፕ ለኮሮና የሰጡት ምላሽ ምስቅልቅሉ የወጣ ነው” ሲሉ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ኦባማ ገለጹ
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራካ ሁሴን ኦባማ “የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላል የያዙት መንገድ ምስቅልቅሉ የወጣ ነው” ሲሉ የአሁኑን የሀገራቸውን አስተዳደር ተችተዋል፡፡ ከቀድሞ የእርሳቸው አስተዳደር ሰዎች ጋር በነበራቸው መግለጫ እንደገለጹት አሁን ላይ የገጠመን ችግር የአንድ ግለሰብ አሊያም የአንድ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ስርዓት ነው ብለዋል፡፡
በቀጣዩ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዴሞክራቶችን የሚወክሉትን ጆ ባይደንን በመደገፍ ትራምፕን መጣል ይገባል ያሉት ባራክ ኦባማ ይህንን ሁሉም እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ከ 3ሺ በላይ የኦባማ አልሙኒ ማህበር አባላት በተገኙበት ባደረጉት ገለጻ በህዳሩ ምርጫ የቀድሞው የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ቀጣዩ የሀገሪቱ መሪ እንዲሆኑ ማገዝና መደገፍ አለብን ብለዋል፡፡
ቀጣዩ ምርጫ በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ ነው ያሉት ኦባማ ምርጫው ከአንድ ግለሰብ ወይም ከአንድ ፓርቲ ባለፈ ራስወዳድነትን፣ ጨካኝነትን፣ መከፋፈልን እና ሌሎችን እንደጠላት የመቁጠር ሃሳብንም ማሸነፍ የምንችልበት ነው ብለዋል፡፡ አሁን ላይ በአሜሪካ የትራምፕና የባይደን ፍጥጫ እየተካረረ መምጣቱ የተነገረ ሲሆን የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት በአንዳንድ ቦታዎች ላይ በተደረገ ድንገተኛ መጠይቅ አሸናፊ እየሆኑ ነውም ተብሏል፡፡
ኦባማ ለባይደን የክብር ኒሻን ሲሸልሙ
ባራክ ኦባማ ፕሬዚዳንቱና አስተዳደራቸው ለኮሮና የሰጡት ምላሽ በጣም የተመሰቃቀለ ነው ብለዋል፡፡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ከሰሞኑ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የተቋቋመውን ግበረ ኃይል እንደሚበትኑ ገልጸው የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ግን ሃሳባቸውን ቀይረው ግብረ ኃይሉ ሥራውን እንደሚቀጥል አስታውዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በምጣኔ ሀብቱ ላይ ትኩረት እንደሚደረግ መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን ባራክ ኦባማ ግን ሁኔታው ሁሉ ምስቅልቅል ያለ ነው ብለዋል፡፡ወረርሽኙ የቻይና ቫይረስ ነው ከማለት አንስቶ ብዙ ሰው የተገኘብን ብዙ ስለመረመርን ነው እስከሚለው የፕሬዚዳንቱ ንግግር ድረስ አሜሪካ ዋጋ እየከፈለች ነው የሚሉ አሉ፡፡ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ንግግር ላይ ኋይት ሃውስ ምንም አስተያየት አልሰጠም ተብሏል፡፡
ምንጭ፡- ሲጂቲኤን