የኢራን ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች በኳታር የዓለም ዋንጫ ላይ መቃወም እንደሚችሉ ተገለጸ
የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ካርሎስ ኪሮዥ የፊፋን ህግ አክብረው ተቃውሟቸውን መግለጽ ይችላሉ ብለዋል
የኳታር የዓለም ዋንጫ የፊታችን እሁድ በዶሃ ይጀመራል
የኢራን ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች በኳታር የዓለም ዋንጫ ላይ መቃወም እንደሚችሉ ተገለጸ፡፡
የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ባለፈው ሰኔ ላይ መካሄድ የነበረበት ቢሆንም የውድድሩ አዘጋጅ በሆነችው ኳታር ከፍተኛ ሙቀት መሆኑን ተከትሎ ውድድሩ ወደ ህዳር ሊዘዋወር ችሏል፡፡
በዚህም መሰረት በአራት ዓመት አንዴ የሚካሄደው ይህ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ ህዳር ላይ የተካሄደ የዓለም ዋንጫ መሆን ችሏል፡፡
የኳታር 2022 የዓለም ዋንጫ የፊታችን እሁድ በሀገሪቱ መዲና በዶሃ የሚጀመር ሲሆን የውድድሩ መክፈቻ ጨዋታ በአዘጋጇ ኳታር እና ኢኳዶር አማካኝነት የፊታችን እሁድ ይደረጋል፡፡
በዚህ ውድድር ላይ ከሚሳተፉ ብሄራዊ ቡድኖች መካከል ኢራን አንዷ ስትሆን አሰልጣኝ ካርሎስ ኪሮዥ ተጫዋቾቻቸው የሀገራቸውን መንግስት መቃወም ከፈለጉ መቃወም ይችላሉ ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በኢራን ከሁለት ወር በፊት የ22 ዓመቷ ማሻ አሚኒ የጠባለች እንስት ሂጃብ አልለበስሽም በሚል በሀገሪቱ ፖሊስ ተያዛ በደረሰባት ድብደባ ህይወቷ አልፏል መባሉን ተከትሎ ተቃውሞ ተነስቷል፡፡
በኢራን የተለያዩ ከተሞች እና በውጭ ሀገራት ያሉ ኢራናዊያን ተቃውሟቸውን በመግለጽ ላይ ሲሆኑ በኳታር በሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ላይ የሚሳተፉት የኢራን ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾችም መቃወም እንደሚችሉ አሰልጣኛቸው ገልጸዋል፡፡
አሰልጣኙ እንዳሉት የብሄራዊ ቡድኑ ተጫዋጮች የፊፋን ህግ አክብረው መቃወም ይችላሉ ሲሉ ከብዙሃን መገናኛዎች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል ተብሏል፡፡
የኢራን መንግስት በበኩሉ ማሻ አሚኒ ህይወቷ ያለፈው ከዚህ በፊት በነበረባት የልብ ህመም ምክንያት እንጂ ፖሊስ በደረሰባት ድብደባ አይደለም ሲል ከዚህ በፊት ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል፡፡
በኢራን ተቃውሞዎች እንዲስፋፉ ምዕራባዊያን ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነ የገለጸችው ቴህራን ዜጎች ከዚህ ሀገርን ከሚጎዳ ተቃውሞ እንዲታቀቡም አሳስባለች፡፡