የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ለፖለቲካዊ ችግሮች የመፍትሄ አካል ለመሆን በማሰብ ስልጣን መልቀቃቸውን ገልጸው ነበር
ከሶስት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ የተለያዩ ቦታዎች የፖለቲካ ተቃውሞ አንቅስቃሴዎች መበርታታቸውን ተከትሎ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ከስልጣን መልቀቃቸው ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተፈጠሩ ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ሂደት “የመፍትሄው አካል”ለመሆኑ በመፈለግ ስልጣን ለመልቀቅ እንደወሰኑ ገልጸው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም የስልጣን መልቀቂያ ማመልከቻቸውን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማስገባታቸው ይታወሳል፡፡
በወቅቱ በነበረው ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ ጫና ውስጥ የገባው መንግስት፣ላለፉት 50 ዓመታት የፖለቲካ አስረኞችን ለማሰሪያነት እና ለማሰቃያነት ይውል የነበረው በተለምዶ ማዕከላዊ በመባል የሚታወቀው እስር ቤት ወደ ሙዚየምነት እቀይራለሁ ብሎ ወስኖ ነበር፡፡
ይህ በተባለ በዓመቱ ማለትም የካቲት 2011 ዓ.ም ላይ ለተወሰኑ ቀናት ይህ እስር ቤት ህዝብ እንዲጎበኘው ለህዝብ እይታ ክፍት ሆኖ ነበር
በወቅቱም እስር ቤቱን የጎበኙ ሰዎች ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት ስፍራው ለጎብኚዎች ክፍት መደረጉ መልካም ሆኖ ሳለ የማሰቃያ ቦታዎቹ በቀለም ተቀብተዋል፤ አሁን ላይ ሲታይ ምኑም የማሰቃያ ቦታ አይመስልም የሚሉ አስተያየቶች ተደምጠው ነበር።
ይሁንና ይህ ስሙ በመጥፎ የሚነሳው እስር ቤት ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ተዘግቷል፤ባደረግነው የመስክ ምልከታም አሁን ድረስ ዝግ ነው።
አል አይን ኒውስ መንግስት እስር ቤቱን ወደ “ሙዚየምነት እቀይራለሁ” ካለ በኋላ ለምን እስካሁን አልቀየረውም፤ ለምንስ ክፍት አላደለገውም ? የሚል ጥያቄን ይዞ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ወደተባሉ የመንግስት ተቋማት ጠይቋል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ከንቲባ ጽህፈት ቤት እና የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው ተቋማት ናቸው።
የፈዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ቃለ አቀባይ አቶ ጀይላን አብዲ እንዳሉት ማዕከላዊ እስር ቤት አሁን ድረስ ንብረትነቱ የኮሚሽኑ መሆኑን ገልጸዋል። ይሁንና ከሶስት ዓመት በፊት ወደ ሙዚየምነት እንዲቀየር መንግስት ቢወስንም እስር ቤቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር እንደሚረከበው አሳውቆ ነበር ብለዋል።
ይሁንና ከተማ አስተዳድሩ እስካሁን ድረስ ማዕከላዊ አስር ቤትን አልተረከበም ሲሉ አቶ ጀይላን ተናግረዋል።አቶ ጀይላን አሁን ላይ በማእከላዊ እስርቤት የወንጀል ምርምር እየተደረገ አለመሆኑን አስታውቀዋል፡፡
አዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ በበኩሉ የማዕከላዊ እስር ቤት ጉዳይን እንደማያውቀው አስታውቋል።
በቢሮው የኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ወርቁ መንገሻ በከተማዋ 17 ሙዚየሞችን በማስተዳደር ላይ መሆናቸውን ገልጸው ማዕከላዊ አስር ቤት ወደ ሙዚየምነት ይቀየራል ስለመባሉ መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ከንቲባ ጽህፈት ቤት እና ፕረስ ሴክሬታሪያት ስለማዕከላዊ እስር ቤት ወደ ሙዚየምነት መቀየር ጉዳይ የጀመረው ስራ ይኖር ይሆን? በሚል ምላሽ እንዲሰጡን በስልክ እና በአካል ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም ምላሽ ሊሰጡን አልቻሉም።