ለ80 አካል ጉዳተኞች ሰው ሰራሽ አካል በነጻ የሰራው በጎ ፈቃደኛ
በጎፈቃደኛው እርዳታውን የሚያደርገው ገንዘብ በመለመን ነው
የሰው ሰራሽ አካል ድጋፍ አገልግሎት በኢትዮጵያ የ60 አመት እድሜ ቢያስቆጥርም እንደሌላው አለም እንዳልዘመነ በጎ ፈቃደኛው ይገልጿሉ
አቶ ሰለሞን አማረ ይባላል። ነዋሪነቱ በእንግሊዝ ሀገር ለንደን በማድረግ ፌስቡክ እና ሌሎች የማህበራዊ ትስስር ገጾችን በመጠቀም ገንዘብ በማሰባሰብ በተለያዩ ምክንያቶች አካላቸውን ያጡ ዜጎችን እንዲራመዱ፤ስራቸውን በሚገባ ማከናወን የሚያስችሉ ሰው ሰራሽ አካሎችን በመስራት ይታወቃል።
ስራው ፈታኝ ቢሆንም አካል ጉዳተኛ የሆኑ ህጻናትን፤ወታደሮችን፤መምህራንን፤የጤና ባለሙያዎችን እናቶች እና አዛውንቶችን ሰው ሰራሽ አካል ድጋፍ በማድረግ ጉዳቶችን ለመቀነስ እየሞከሩ መሆናቸውን አቶ ሰለሞን ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቃል ምልልስ ተናግረዋል፡፡
- የአካል ጉዳተኞች ቀን
- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር የዘንድሮውን የጀርመን አፍሪካ ሽልማት አሸነፉ
- የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ኃላፊ በኢትዮጵያ ቆይታቸው የትግራይ እና አማራ ክልሎችን እንደሚጎበኙ ገለጹ
አቶ ሰለሞን ይህ ድጋፍ ለብቻ የሚሰራ ባለመሆኑ ስራው የህክምና ባለሙያ እገዛም እንደሚያስፈልገው ገልጿል፡፡ በተለይም ህጻናት ጋር አጥንታቸው በየጊዜው ስለሚያድግ ከሰው ሰራሹ አካል ጋር ግጭት እየፈጠረ ህመም ይፈጥራል፤ ስለዚህ በየጊዜው ከሚያድገው አጥንታቸው ጋር ሰው ሰራሹን አካል ማስተካከል ይጠይቃል፤ ይህ ደግሞ የህክምና ባለሙያዎችን ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል አቶ ሰለሞን።
አካላቸው በተለያዩ ምክንያቶች የጎደለባቸው እድሜ ልካቸውን ከቤት ወጥተው ያማያውቁ፤ በሰው እርዳታ የሚንቀሳቀሱ፤ተንቀሳቅሰው የልባቸውን ማድረግ ያልቻሉ ብዙ ኢትዮጵያዊያን አሉ እነዚህን ዜጎች በቀላሉ የአካል ድጋፍ አድርገንላቸው መርዳት እንፈልጋለን ይላሉ ሰለሞን ።
ይሄንን ስራ ተቋማዊ ማድረግ እንፈልጋለን፤ ቴክኖሎጂውን ማስተዋወቅ ለሰፊው ህዝብ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ተቋም ጋር ለመስራት በጥረት ላይ መሆናቸውንም አቶ ሰለሞን ጠቅሰዋል።
ዋና መቀመጫውን ለንደን ያደረገ እና ለአካል ጉዳተኞች ሰው ሰራሽ አካል ድጋፍ ለማድረግ ያለመ ፕሮስተቲክስ ኦርቴቲክስ ፋውንዴሽን (ኦፕፋ) የተሰኘ ተቋም ከጓደኞቻቸው ጋር ማቋቋማቸውን አቶ ሰለሞን ነግረውናል።
ከመጭው ጥር በኋላም ይሄንን ተቋም ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ በማድረግ አገልግሎት መስጠት ብቻ ሳይሆን ዘመናዊ የፕላስቲክ ቴክኖሎጂ እውቀት ማሳደግ እንፈልጋለን ብለዋል።
ወደ ኢትዮጵያ ከገባ 60 ዓመትያስቆጠረው የፕላስቲክ የሰው ሰራሽ አካል ድጋፍ አገልግሎት በዓለማችን በጣም የዘመነ ቢሆንም ኢትዮጵያ ውስጥ ግን እድገት አለማሳየቱን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል፡፡
በዚህ ፋውንዴሽን አማካኝነት አውሮፓ ያሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ህክምና ሳይንስን ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት እና ማሳደግ እንፈልጋለን ብለዋል አቶ ሰለሞን።
በውጭ ሀገራት በተለይም በአውሮፓ አንድ የሰው ሰራሽ እግር ድጋፍ ለማግኘት በትንሹ 8 ሺህ ዩሮ ይፈጃል የሚሉት አቶ ሰለሞን ቢቻል በነጻ ካልተቻለ በቅናሽ ዋጋ አገለግሎቱን ለሚፈልጉ ሰዎች የመስጠት እና ባለሙያዎችን ማሰልጠን አቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ላለፉት 45 ዓመት በጦርነት ወስጥ ናት የሚሉት አቶ ሰለሞን በጽኑ ህመሞች ምክንያት አካላቸውን የሚያጡትን ዜጎች ጨምሮ በጦርነት እና በአደጋዎች አካላቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር ቀላል አለመሆኑን ተናግረዋል።
እስካሁን ለ80 ሰዎች የሰው ሰራሽ አካል ድጋፍ ማድረጋቸውን የተናገሩት አቶ ሰለሞን ሁሉንም ሰዎች በነጻ አገልግሎቱን አግኝተዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መልክዓምድር አቀማመጥ ወጣ ገባ ቢሆንም አንድ ሰው ሰራሽ እግር ከሁለት አስከ 5 ዓመት ድረስ አገልግሎት መስጠት የሚችል ሲሆን እንደጉዳቱ መጠን በቀጣይ ደግሞ ተጨማሪ ድጋፍ ይደረጋል ይላሉ አቶ ሰለሞን።
ድጋፉን ለሚፈልጉ ዜጎች የሰው ሰራሽ አካሉ እየተሰጠ ያለው ከበጎ ፈቃደኞች በማህበራዊ ሚዲያ እና በአካል ከሚያውቋቸው ሰዎች በማሰባሰብ እንደሆነ አቶ ሰለሞን ተናግረዋል።
ከጥቂት ተቋማት ውጪ የመንግስት ተቋማት እስካሁን የተደራጀ ድጋፍ እያደረጉላቸው እንዳልሆነ የተናገሩት አቶ ሰለሞን የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እና አቤት ሆስፒታል ድጋፍ ካደረጉላቸው ተቋማት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
በኢትዮጵያ ከጠቅላላው ህዝብ ቁጥር ውስጥ 17 ነጥብ 5 ያህሉ አካል ጉዳተኛ ሲሆን ከዚህ ወስጥ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት የሰው ሰራሽ አካል ድጋፍ የሚፈልጉ እንደሆኑ የመንግስታቱ ድርጅት ሪፖርት ያስረዳል።
ይሄንን ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሰረተ ልማት በኢትዮጵያ የሌለ ሲሆን መንግስት የራሱን ሃላፊነት እንዲወጣ አቶ ሰለሞን ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ የሰው ሰራሽ አካል ድጋፍ ለሚፈልጉ ሰዎች አገልግሎት ለመስጠት በትንሹ 6ሺህ ባለሙያ ቢያስፈልግም አገልግሎቱን እየሰጡ ያሉ ባለሙያዎች ግን 60 ብቻ ናቸውም ብለዋል።
የሰው ሰራሽ ድጋፍ የሚሰጡ ባለሙያዎችን በዲፕሎማ ሲያሰለጥን የነበረው እና በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ የሚገኘው ማሰልጠኛ መዘጋቱ እንዳሳዘናቸውም አቶ ሰለሞን ተናግረዋል።
ይህ ተቋም የግድ መከፈት አለበት የሚሉት አቶ ሰለሞን ዘርፉ ድጋፉን የሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያንን ከመርዳት ባለፈ የፕላስቲክ ቴክኖሎጂ ህክምናን በማስፋፋት አፍሪካዊ ወንድሞቻችን ወደ እኛ እየመጡ እንዲታከሙ በማድረግ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማግኛ ማድረግ እንደሚቻል ገልጸዋል።
ወደዚህ ሙያ እንዴት ለትገባ ቻልክ? በሚል ላነሳንለት ጥያቄም በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በህክምና ሙያ ለመማር ኮሌጁን በተቀላቀለበት ጊዜ መሆኑን ነግሮናል።
ጊዜውን ሲያስታውስም “ወቅቱ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወደ ጦርነት የገቡበት ወቅት ነበር። ብዙዎች በጦርነቱ ቆስለው አካላቸውን አጥተው ሲቸገሩ በማየታቸው ወደዚህ ሙያ በዚያው ገባሁበት፤ይሄው አሁንም ድረስ ይህ አልተወኝም አሁንም ጦርነት ውስጥ ነን የተጎዱ ሰዎችን በቻልኩት መጠን መርዳቴን እቀጥላለሁ” ብለዋል።
የሰው ሰራሽ አካል ድጋፉን ለመስጠት መስፈርታችን ወታደሮች ከሆኑ፤የጉዳቱ መጠን ከፍተኛ ከሆነ ለምሳሌ ሁለቱንም እግር ወይም እጃቸውን ካጡ፤ህጻናት ከሆኑ እና ሌሎችንም ምክንያቶች መነሻ በመድረግ እንደሚሰሩም አቶ ሰለሞን ነግረውናል።
ከሚኖርበት ለንደን ወደ አዲስ አበባ እየተመላለሰ ተጎጂዎችን በመርዳት ላይ የሚገኘው አቶ ሰለሞን አማረ አሁን የተጎጂዎች መጨመር እና መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ላይ መሆኑን ተከትሎ በቋሚነት ኑሯቸውንን በኢትዮጵያ ለማድረግ እያሰቡ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡