ከምርጫ ታዛቢው አሟሟት ጋር በተያያዘ ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር በመሆን ምርምራ እየተደረገ ነው
ጆን ማርሽ ትናንት ጠዋት ነው በራዲሰን ብሉ ሆቴል የመኝታ ክፍሉ ውስጥ ሞቶ የተገኘው
በሟች ሰውነት ላይ ምንም አይነት የአካል ጉዳትና ቁስለት አለመገኘቱን ፖሊስ አስታውቋል
በውጭ አገር ታዛቢው የአሟሟት ሁኔታ ላይ ምርምራ እየተደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ “ትናንት በራዲሰን ብሉ ሆቴል አሜሪካዊ ዜጋ በመኝታ ክፍሉ ሕይወቱ አልፎ ተገኝቷል” ብለዋል።
የሆቴሉ የጽዳት ሠራተኛ ትናንት ጠዋት 1፡00 ገደማ አሜሪካዊው ያረፈበትን የመኝታ ክፍል ለማጽዳት ስትገባ ያየችውን ነገር ለፖሊስ ጥቆማ መስጠቷን ገልጸዋል።
ፖሊስ መረጃውን እንዳገኘ ወደ ስፍራው መንቀሳቀሱንና አሜሪካዊው ከአልጋው ላይ ወደ መሬት ወድቆ ሕይወቱ አልፎ እንደተገኘ አመልክተዋል።
በሟች ኪስ ውስጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ልዩ የምርጫ ታዛቢ ወረቀት (ባጅ)፣ የተለያዩ መታወቂያዎችና መንጃ ፈቃድ መገኘታቸውን ተናግረዋል።
መንጃ ፈቃዱ “በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ብሔራዊ የድራይቪንግ ላይሰንስ” የሚል እንደሆነም አስረድተዋል።
በተጨማሪም አሜሪካዊው የሚጠቀምባቸው “በርካታ” መድሃኒቶችን ፖሊስ ማግኘቱንና “ምናልባት ሁኔታው ሲታይ በተፈጥሮ የሞተ እንደሚመስልና ነገር ግን ትክክለኛው መረጃ ከአስከሬን ምርመራ ውጤት በኋላ የሚታወቅ ነው” ብለዋል ዳይሬክተሩ።
“በአሜሪካዊው ዜጋ ሰውነት ላይ ምንም አይነት የአካል ጉዳትና ቁስለት አልተገኘም” ነው ያሉት ኮማንደር ፋሲካ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንና በአዲስ አበባ ከሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ጋር በመሆን በአሜሪካዊው ዜጋ አሟሟት ላይ ምርምራ እያደረጉ እንደሆነም ገልጸዋል።
ፖሊስ አጠቃላይ የምርመራውን ውጤት በቀጣይ ይፋ እንደሚያደርግም አክለዋል።
የካርተር ሴንተር ፕሮግራም በኢትዮጵያ በይፋዊ የትዊተር ገጹ ዛሬ ማለዳ ባወጣው መረጃ በራዲሰን ብሉ ሆቴል ሕይወቱ ያለፈው የተቋሙ የአዲስ አበባ የፕሮግራም ስራ አስኪያጅ ዶክተር ጆን ማርሽ መሆኑንና ሕይወቱም ትናንት እንዳለፈ ገልጿል።
"የካርተር ሴንተር በኢትዮጵያ በጆን ማርሽ ድንገተኛ ሞት ከፍተኛ ሐዘን ተሰምቶናል፤ ጆን ማርሽ የኢትዮጵያ እውነተኛ ወዳጅ ነው" ብሏል በመግለጫው።
የካርተር ሴንተር ለዶክተር ጆን ማርሽ ወዳጆች መጽናናትን ተመኝቷል።