ኢትዮጵያ በለንደን ማራቶን በሁለቱም ጾታዎች ድል ቀንቷታል
አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው የሴቶች ማራቶን ውድድርን ስታሸንፍ ልዑል ገብረስላሴ በወንዶች ማራቶን ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል
በውድድሩ ተጠብቆ የነበረው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ አምስተኛ ሆኖ አጠናቋል
ኢትዮጵያ በለንደን ማራቶን ውድድር የወርቅ ፣ብር እና ነሀስ ሜዳሊያዎችን አገኘች፡፡
በየዓመቱ በሚካሄደው ለንደን ማራቶን ውድድር ላይ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች የተሳተፉ ሲሆን አትሌት ያለምዘርፍ የኃላው የለንደን ማራቶን የሴቶች ውድድርን አሸንፋለች፡፡
አትሌት ያለምዘርፍ ርቀቱን 2:17:25 ሰዓት በመግባት ያሸነፈች ሲሆን አትሌቷ በውድድሩ ወቅት ወድቃ የነበር ቢሆንም ተነስታ ፍጥነቷን ጨምራ ውድድሯን በጥሩ ብቃት አሸንፉለች::
በዚህ ውድድር ላይ እንደምታሸንፍ ትልቅ ግምት ተሰጥቷት የነበረችው ከንያዊቷ አትሌት ጆይስሊን ኪፕሶጊ ሁለተኛ ደረጃን ስትይዝ አትሌት አለሙ መገርቱ ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች።
በወንዶች ተመሳሳይ ውድድር ደግሞ ኬንያዊው አሞስ ኪፕሩፕ ውድድሩን 2፡04፡39 በሆነ ሰዓት በአንደኝነት ሲያሸንፍ ልኡል ገብረስላሴ ከኢትዮጵያ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል፡፡
ቤልጂየማዊው በሽር አብዲ ደግሞ ውድድሩን በሶስተኝነት በማጠናቀቅ ተጠባቂው የለንደን ማራቶን ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡
በዚህ ውድድር ላይ ለማሸነፍ ወደ ለንደን ተጉዞ የነበረው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ አምስተኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡
በእንግሊዛውያኑ አትሌቶች ክሪስ ብራሸር እና ጆን ዲስሌይ በፈረንጆቹ 1981 የተመሰረተው ለንደን ማራቶች በየዓመቱ አንዴ የሚካሄድ ዓለም አቀፍ ውድድር ነው፡፡
በዚህ ውድድር ላይ በአጠቃላይ 40 ሺህ ዜጎች የተሳተፉ ሲሆን ውድድሩን አፍሪካዊያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች አሸንፈዋል፡፡