ሶኒ “ዎክማን” የሙዚቃ ማዳመጫ ዳግም ወደ ገበያ ሊመለስ ነው አለ
“ዎክማን”የሙዚቃ ማዳመጫ በተለይም በ80ዎቹ እና 90ዎቹ ትውልዶች ዘንድ ትልቅ ትውስታ አለው
“ዎክማን NW-A306” የባትሪ እድሜ እስከ 36 ሰዓት ይቆያል የተባለ ሲሆን፤ አንድሮይድ 12 ይጠቀማል
የ80ዎቹ እና የ90ዎቹ ትውልድ በጣም ታዋቂ የሙዚቃ ማዳመጫ የነበረው “ዎክማን” ዳግም ወደ ገበያ ሊመለስ መሆኑን ሶኒ ኩባንያ አስታውቋል።
“ዎክማን” የሙዚቃ ማዳመጫ በቴክኖሎጂ እድገት እና ስማርት ስልኮች ብቅ ማለት ጋር ተያየዞ እየጠፋ የሄደ ቢሆንም፤ የጃፓኑ ሶኒ ኩባያ በዎክማን ላይ ስር ነቀል ለውጦችን በማድረግ በአዲስ ቴክኖሎጂ ይዞ መምጣቱን አስታውቋል።
ሶኒ ኩብንያ “ዎክማን” የሙዚቃ ማዳመጫ ቴፕን ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ካስተዋወቀ ከ40 ዓመታት በኋላ አዲሱን “NW-A306” ዎክማን ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ አዲሱ ዎክማን ከዚህ ቀደም በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደውት ይጠቀሙት ከነበረው ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው ተነግሯል።
አዲሱ “ዎክማን NW-A306” ተጠቃሚዎች ኢንተርኔት ተጠቅመው ሙዚቃ በቀጥታ እንዲያጫውቱ አሊያም ዳወንሎድ አድርገው እንዲያዳምጡ ያስችላል የተባለ ሲሆን፤ ይህንን ለማድረገም እንደ ዩትዩብ እና ስፖቲፊ ያለ መተግበሪያዎችን እና የሙዚቃ ማጫወቻ ድረ ገጾችን መጠቀም የሚያስችል ነው።
“ዎክማን NW-A306” አንድሮይድ አኦፕሬቲንግ ሲስተም የሚጠቀም ሲሆን፤ ጠቃሚ የሆኑ መተግበሪያዎችን እንዲሁም ግጎል ክሮምን ከፍቶ ለመጠቀምም ያስችላል ተብሏል።
ሶኒ ስለ አዲሱን ዎክማን አስመልክቶም፤ "በሚያምረው የሙዚቃ ማጫወቻ ከፍተኛ ጥራት ባለው ድምጽ ተዝናኑ ፤የሚወዱትን ሙዚቃ እያወረዱ ይዝናኑበት” ብሏል።
አዲሱን ዎክማነ በዋይፋይ ተጠቅመን ከኢንተርኔት ጋር ማገናኘት የምንችል ሲሆን፤ ከኮምፒውተራችን ጋር በማገናኘትም የምንወደውን ሙዚቃ ማስተላለፍ እንችላለን ተብሏል።
“ዎክማን NW-A306” የባትሪ እድሜ እስከ 36 ሰዓት ይደርሳል የተባለ ሲሆን፤ አንድሮይድ 12 እንደሚጠቀም እንዲሁም በሰማያዊ እና በጥቁር ቀለማት ለገበያ መዘጋጀቱም ታውቋል።
ዋጋውስ ካላችሁ፤ ለአዲሱ “ዎክማን NW-A306” የተቆረጠለት ዋጋ 430 የአሜሪካ ዶላር አሊያም 22 ሺህ ብር ገደማ ነው።