በስልካችን ላይ ሊኖሩን የሚገባና የሚጠቅሙን መተግበሪያዎች የትኞቹ ናቸው?
በአንድሮይድ ስልኮች የሚገኙ መተግበሪያዎች ቁጥር ከ2 ነጥብ 7 ሚሊየን ደርሷል
የእለት ተዕለት ህይወትን የሚያቀሉ፣ ስራን የሚያቀላጥፉና መዝናናትን የሚፈጥሩ መተግበሪያዎች እንዳሉ ሁሉ ተጠቃሚው ላይ ችግር የሚፈጥሩትም ቀላል አይደሉም
የአንድሮይድ ኦፕሬቲንግ ሲስተምን በሚጠቀሙ ስልኮች ላይ የሚገኙ መተግበሪያዎች ቁጥር ከ2 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ መድረሳቸው ይነግራል።
በመላው አለም ከ6 ቢሊየን በላይ የስማርት ስልክ ተጠቃሚዎች ያሉ ሲሆን፥ በአመት ከ200 ቢሊየን በላይ መተግበሪያዎች ይጫናሉ።
እነዚህ መተግበሪያዎች የእለት ተዕለት ህይወትን የሚያቀሉ፣ ስራን የሚያቀላጥፉና መዝናናትን የሚፈጥሩ ናቸው።
አፕ ስቶር ላይ ከሚገኙ መተግበሪያዎች ውስጥ ብናወርዳቸውና ብንጠቀምባቸው ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ይኖራቸዋል ያልናቸውን እንጠቁማችሁ፦
Sketchbook
በስዕልና ዲዛይን ላይ ለመስራት ፍላጎት ያላችሁና ባለሙያዎች ስኬችቡክን ይጠቀሙበት። በነጻ የምናገኘው ስኬችቡክ ወረቀትን ከብክነት የታደገ ምርጥ መተግበሪያ ነው ይላል አንድሮይድፖሊስ የተሰኘው ድረገጽ።
Amazon Kindle
ኤሌክትሮኒክ መጽሃፍትን የማንበብ ልምድ ካዳበሩ ደግሞ ኪንድል ቁጥር አንድ ተመራጭ መተግበሪያ ነው። የአማዞን መተግበሪያ የሆነው ይህ ኪንድል እጅግ ውድ የሆኑ መጽሃፍትን፣ ጋዜጦችንና መጽሄቶችን በኦንላይን ለመግዛትና ለማንበብ የሚያስችል ነው።
Slack
ስላክ በቢዝነሱ አለም ያሉ ሰዎችን የሚያገናኝና ስራን የሚያቀል መተግበሪያ ነው። በመላው አለም የሚገኙ በንግድ አለም የሚገኙ ስዎች እንደ አንድ ቡድን እንዲሰሩ እድል የሚፈጥር መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያ ነው።
ZOOM Cloud Meetings
የቪዲዮ ስብሰባን ለማድረግ ተመራጭ የሆነው ዙም አሁንም ተመራጭ መተግበሪያ ሆኖ ቀጥሏል። እስከ 1 ሺህ ሰዎችን በአንዴ ከያሉበት የሚያገናኘው ዙም በነጻ (እስከ 40 ደቂቃ) እና በክፍያ አማራጭ የቀረበ ሲሆን፥ ተአማኒ የመገናኛ መድረክ ነው። የኮቪድ 19 መከሰት ይበልጥ ተፈላጊነቱን የጨመረው ይህ መተግበሪያ ከኮቪድ ወረርሽኝ ማግስትም ተፈላጊነቱ መጨመሩ ተነግሯል።
Samsung Internet Browser
የሳምሰንግ የኢንተርኔት ብሮውዘር ከክሮም በተሻለ ፈጣን ፍለጋን ለማድረግ እንደሚያስችል አንድሮይድ ፖሊስ ድረገጽ ያነሳል። በክሮም ላይ የሚታየውን መንቀራፈፍ እና አላስፈላጊ የፋይሎች ጥርቅም የሚያስቀረው ሳምሰንግ ኢንተርኔት ብሮውዘር ከሳምሰንግ ውጭ ባሉ ስልኮችም አገልግሎት ላይ መዋል ይችላል።
Tor Browser
የጎግል ፍለጋ ውጤታችሁ ሚስጢራዊነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ከፈለጋችሁ ቶር ብሮውዘር ተመራጭ ነው። የፍለጋ ውጤቶችን ከሶስተኛ ወገን ስለላ የሚታደገው ይህ መተግበሪያ በነጻ የቀረበ ሲሆን ከቪ ፒ ኤን በተሻለ መልኩ የኢንተርኔት ደህንነትን ለማረጋገጥ ያግዛልም ነው የተባለው።
Khan Academy
በእውቅ ባለሙያዎች የተዘጋጁ ኦንላይን ኮርሶችን ለመውሰድ የካን አካዳሚ መተግበሪያን ማውረድ እንዳይዘነጉ። በፈለጉት ዘርፍ የተዘጋጁ ማጣቀሻ መጽሃፍትን፣ ቪዲዮዎች እና አጫጭር ፈተናዎችን ያካተተው መተግበሪያው፥ በነጻ የቀረበ ሲሆን ለተማሪዎችም ሆነ ለመምህራን ሰፊ እድሎች አሉት።
Duolingo
አዲስ ቋንቋን መማር የምትፈልጉ ደግሞ ዶሊንጎን ይሞክሩት። ከ35 በላይ ቋንቋዎችን ያካተተው ዶሊንጎ ከሀገር ሀገር ለጉብኝትም ሆነ ለስራ ለሚንቀሳቀሱ ሰዎች በአጭር ጊዜ የመግባቢያ ቋንቋዎችን መገብያ መድረክ ነው። የየእለት ልምምዶችን እየመዘገበ ውጤት መስጠቱም በአካል የመማር አይነት ስሜት ይፈጥራል። ችግሩ ግን ከ14 ቀናት የነጻ ሙከራ በኋላ ክፍያ መጠየቁ ነው።