ከእስር ለማምለጥ ለ20 አመታት መስማት የተሳነው መስሎ የኖረው ቻይናዊ ተያዘ
ጎረቤቱን ገድሎ ከመኖሪያ ቀዬው የጠፋው ግለሰብ ያለፈ ታሪኩን ለመደበቅ በምልክት ቋንቋ ሲግባባ ቆይቷል
በቅርቡ ከሌላ ግለሰብ ጋር ተጣልቶ በፖሊስ በቁጥጥር ስር ሲውል የተነሳው ምስል ግን አጋልጦታል
በግድያ ወንጀል ሲፈለግ የነበረው ቻይናዊ ለ20 አመታት መስማት የተሳነው መስሎ ቢቆይም በቁጥጥር ስር ውሏል።
ሻኦ በሚል አጭር ስሙ የሚታወቀው ግለሰብ በግንቦት ወር 2004 ነበር ከጎረቤቱ ጋር ተጣልቶ በአካፋ መትቶ የገደለው።
ደመ ሞቃቱ የሺያንያንግ ከተማ ነዋሪ በሁኔታው ተደናግጦ በዚያው ምሽት ሚስቱንና የ11 አመት ልጁን ትቶ ማምለጡንም ፖሊስ ይገልጻል።
ሻኦ በፖሊስ ታድኖ እንዳይያዝ በማሰብም በፉጂያን ግዛት አንሺ በተባለ አካባቢ ጫካ ውስጥ ፍራፍሬ እየለቀመ በመሸጥ የዱር ህይወትን መኖር ይጀምራል።
የቀደመ ህይወቱን በተመለከተ ለማንም ትንፍሽ ላለማለትም መስማት የተሳነው መምሰልን መርጦ ለሁለት አስርት አመታት በምልክት ቋንቋ ሲግባባ ቆይቷል።
ፈገግ ከማለት ውጪ አንድም ቀን ለሰዎች በንግግር ምላሽ ሳይሰጥም ከሚያሳድደው ወንጀል ለማምለጥ ቢሞክርም በቅርቡ በተሰደደበት አካባቢ ከሰዎች ጋር ተጣልቶ በፖሊስ በቁጥጥር ስር ሲውል የተነሳው ምስል የፈራው እንዲደርስ አድርጎታል።
ግለሰቡ ባለፉት 20 አመታት ሚስትና ልጁን ሊጠይቅ መምጣቱ አይቀርም በሚል ሲጠባበቅ የነበረው የቻይና ፖሊስ ምስሉን ተፈላጊ ወንጀለኞች በሚቀመጡበት ድረገጽ አስገብቷል።
ሻኦ ባለፈው ወር ከተፈጠረው ጸብ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ሲውል የተነሳው ምስልም በወንጀል ይፈለጋል ተብሎ በብሄራዊ የመረጃ ቋት ውስጥ ካለው ተመሳስሎ ተገኝቷል።
ግለሰቡ የተያዘበት ግጭት ቀላል በመሆኑ መለቀቁን ተከትሎ ፖሊስ ወደሚኖርበት ተራራማ ስፍራ ያመራል።
ለ20 አመታት መስማት እንደማይችል ለሚያስመስለው ሻኦ በጽሁፍ “የሺያንያንግ ከተማ ነዋሪ ነበርክ ወይ?” የሚል ጥያቄ አቅርቦም ሻኦ “አዎ” የሚለው ምላሽ ላይ አመላክቷል።
“ለ20 አመታት ሚስጢሬን ይዤ ቆይቻለሁ፤ ለማበድ የተቃረብኩ ያህል እየተሰማኝ ነበር” ሲልም ለአመታት ከወንጀሉ ለማምለጥ ያደረገውን ሙከራ በዝርዝር አስረድቷል።
ቻይናዊው ወደቀደመ መንደሩ በማቅናትም ከ20 አመት በፊት ጎረቤቱን የገደለበትን ቤት ሳይረሳ ማሳየቱን ኦዲቲ ሴንትራል የቻይና መገናኛ ብዙሃንን ጠቅሶ አስነብቧል።
ሻኦ ከግድያ ወንጀሉ በተጨማሪ ቤተሰቡን ትቶ ከፖሊስ ለመሰወር ባደረገው ሙከራ ተደራራቢ ክሶች ቀርበውበት ቀሪ ህይወቱ በማረሚያ ቤት እንደሚሆን ተገልጿል።