አሜሪካ ተኩስ አቁሙን በሚያፈርሰው ኃይል ላይ ማዕቀብ ልትጥል እንደምትችል ገልጻለች
በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ከባድ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን ተመድ ገልጿል።
ተመዱ እንደገለጸው በሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ህጻናት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል።
ሁለቱ ተፋላሚዎች ከቀናት በፊት በደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር አደራዳሪነት ለሰባት ቀናት ተኩስ ለማቆም ተስማምተው ነበር።
የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት መረጃ እንደሚያመለክለው ተኩሱ በድጋሚ ያገረሸው ሁለቱ ኃይሎች ይደረጋል ተብሎ ከሚታሰበው ድርድር በፊት የበላይነት ለማግኘት ነው።
ምንም እንኳን ተፋላሚ ኃይሎቹ ተደጋጋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ቢደርሱም ስምምነቱን እየጣሱ ተጨማሪ ቦታ ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።
የሱዳን ጦር ትናንት በከፈተው ጦርነት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ከያዘው የማእከላዊ ካርቱም ለማራቅ ጥቃት ከፍቶ እንደነበር ሮይተርስ ዘግቧል።
የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት ዳይሬክተር ሄንስ እንደገለጹት ሁለቱም ኃይሎች ጦርነቱን እናሸንፋለን ብለው እንደሚያምኑ ለመደራደር ብዙም ዝግጁ እንዳልሆኑ ተናግረዋል።
አሜሪካ ተኩስ አቁሙን በሚያፈርሰው ኃይል ላይ ማዕቀብ ልትጥል እንደምትችል ገልጻለች።
በሱዳን በተቀሰቀሰው ጦርነት እስካሁን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲሞቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ሀገራቸውን ለቀው ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል።
በሱዳን የተቀሰቀሰው ጦርነት ሦስተኛ ሳምንቱን እያገባደደ ነው።