የጦርነቶችና ቀጠናዊ ውጥረቶች መበራከት የአለም አቀፍ የጦር መሳርያ አምራች ኩባንያዎችን ገበያ አድርቷል
ባለፈው አመት ብቻ 100 አለም አቀፍ ጦር መሳርያ አምራቾች 632 ቢሊየን ዶላር ግምት ያላቸው መሳርያዎችን ሽጠዋል
የአሜሪካ ኩባንያዎች ከአለም አቀፍ የጦር መሳርያ ሽያጭ ትርፍ ግማሹን ይጋራሉ
በአለም አቀፍ ደረጃ እየተበራከቱ የሚገኙ ጦርነት እና ቀጠናዊ ውጥረቶች ለጦር መሳርያ አምራች ኩባንያዎች ገበያ መድራት መንስኤ መሆኑ ተገልጿል።
የሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት ፣ የመካከለኛው ምስራቅ ግጭቶች እንዲሁም በእስያ እና በአፍሪካ የሚገኙ ውጥረቶች ለጦር መሳርያ ሽያጭ መበራከት ዋነኛ ምክንያት ተደርገው ተወስደዋል።
የስቶኮልም የአለም አቀፍ ሰላም ጥናት ኢንስቲትዩት ሪፖርት እንዳመላከተው በ2023 የመሳርያ አምራቾች ሽያጭ በ4.2 በመቶ ሲጨምሮ 100 ከፍተኛ የጦር መሳርያ አምራች ኩባንያዎች ብቻ 632 ቢሊየን ዶላር ግምት ያላቸው መሳርያዎችን ሽጠዋል፡፡
በ2022 የነበረውን የጦር መሳርያ አቅርቦት ፍላጎት ማሟላት ባለመቻላቸው ዝቅተኛ ገቢ አስመዝግበው የነበሩት ግዙፍ ኩባንያዎች በ2023 የምርት አቅማቸውን በማሳደግ ከፍተኛ ገቢ አግኝተዋል ነው የተባለው፡፡
የፍላጎት መጨመርን ተከትሎ እነዚህ 100 ኩባንያዎች በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው አመት ሁሉም በተናጥል ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አግኝተዋል።
በ2023 የታየው ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ገበያ በ2024 መቀጠሉን የስቶኮልም የአለም አቀፍ ሰላም ጥናት ኢንስቲትዩት ወታደራዊ ወጪ እና የጦር መሳሪያ ምርምር ፕሮግራም ተመራማሪ ሎሬንዞ ስካራዛቶ ተናግረዋል።
በዚህም በ2024 2.4 ትሪሊየን ዶላር ለጦር መሳርያ ግዢ የወጣ ሲሆን 939 ቢሊየን ዶላር የበጀተችው አሜሪካ ቀዳሚዋ ናት ፡፡
ቻይና 373 ቢሊየን ዶላር ፣ ሩስያ 225 ፣ ህንድ 132 ቢሊየን ዶላር ለመከላከያቸው ወጪ በማድረግ በደረጃ የሚገኙ ሀገራት ናቸው፡፡
በጦር መሳርያ ምርት በአለም ቀዳሚዋ የሆነችው አሜሪካ ኩባንያዎች በ2023 ሽያጫቸውን ወደ 2.5 በመቶ ማሳደግ የቻሉ ሲሆን ከአለም አቀፍ የመሳርያ ሽያጭ ገቢም ግማሹን ይጋራሉ፡፡
ከ100 ግዙፍ የጦር መሳርያ አምራቾች መካከል 27ቱ የሚገኙበት አውሮፓ በ0.2 በመቶ አጠቃላይ ሽያጩን አሰድጓል፡፡
ሶስት የእስራኤል አምራቾች በአመቱ በሪከርድ የተመዘገበ 13.6 ቢሊየን ዶላር ግምት ያላቸው መሳርያዎችን ሲሸጡ በተመሳሳይ በቱርክ የሚገኙ በተለይ በድሮን ምርት ላይ የተሰማሩ ሶስት ኩባንያዎች ሽያጭ በ24 በመቶ ስለመጨመሩ ነው የተነገረው፡፡
ድሮኖች ፣ ጥይቶች ፣ የመድፍ እና ታንክ ተተኳሾች ፣ የአየር መቃወሚያ ስርአቶች እንዲሁም የተለያየ አይነት ያላቸው ጠብንጃዎች ከፍተኛ የገበያ ፍላጎት ከተንጸባረቀባቸው የጦር መሳርያ አይነቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡