
ከሰሃራ በታች የሚገኙ ሀገራት 2.2 በመቶ በአለም የጦር መሳሪያ ገበያ ተሳትፎ ነበራቸው
አፍሪካውያን ሀገራት ከበጀታቸው ከፍተኛውን መጠን በመመደብ የጦር መሳሪያ ግዢ ላይ በስፋት እየተሳተፉ እንደሚገኙ አረጋግጫለሁ ያለው የስቶክሆልም አለም አቀፍ የሰላም ጥናት ኢንስቲትውት ነው።
በአለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ የሚገኝውን የጦርነት ስጋት ተከትሎ አለም ወታደራዊ ወጪውን በከፍተኛ መጠን ሲጨምር በ2024 2.4 ትሪሊየን ዶላር ወጪ የተደረገ ሲሆን ከ2023 ጋር ሲነጻጸር በ6.8 በመቶ ጭማሪ ታይቶበታል።
ይህ ስጋት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የሚጎበኛቸው አፍሪካውያን በሀገር ውስጥ ግጭት እና ቀጣናዊ ውጥረት መባባስ ዘመናዊ የጦር መሳሪያን ለመታጠቅ ፣ ወታደራዊ አቅማቸውን ለማጠናከር ጥረት ላይ ናቸው።
በመረጃው መሰረት በፈረንጆቹ 2023 ብቻ የአፍሪካ አህጉር ወታደራዊ ወጪ 51.6 ቢሊየን ዶላር ነበር።
ይህ ወታደራዊ ወጪ ከ2022 አንፃር 22 በመቶ ብልጫ ሲኖረው ከ2014 ደግሞ በ1.5 በመቶ ጨምሯል።
ከአጠቃላዩ የአህጉሩ ወታደራዊ በጀት ወጪ 23.1 ቢሊየን ዶላር ከሰሃራ በታች የሚገኙ ሀገራት ለመከላከያቸው የበጀቱት ነው።
በዚህም ባለፉት አምስት አመታት ብቻ ከሰሃራ በታች የሚገኙ ሀገራት በ2.2 በመቶ በአለም የጦር መሳሪያ ገበያ ላይ ድርሻ ነበራቸው።
ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ናይጄሪያ 20 በመቶ የመከላከያ ወጪዋን በማሳደግ ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ናት።
በተመሳሳይ ዲ አር ኮንጎ ከ105 በመቶ በላይ ወጪን በማሳደግ በአለማችን ከፍተኛውን ወታደራዊ ወጪ ጭማሪን ያደረገች ሀገር ስትሆን አጠቃላይ የመከላከያ በጀቷን 794 ሚሊየን ዶላር አድርሳዋለች።
ኮንጎን በመከተል ወታደራዊ ወጪዋን በ78 በመቶ ያሳደገችው ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ሱዳን 1.1 ቢሊየን ዶላር በ2023 በመመደብ ትጠቀሳለች።
ከ2019 -2023 ባሉት አምስት አመታት ከፍተኛ የጦር መሳርያ ወደ ሀገር ውስጥ ያስገቡ ሀገራት ደረጃ በናይጄሪያ የሚመራ ሲሆን አንጎላ ፣ ሴኔጋል ፣ ማሊ ፣ ዩጋንዳ እና ኢትዮጵያ እስከ ስድስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
በዝርዝሩ ውስጥ ስሟ የተካተተው ኢትዮጵያ በአምስት አመታቱ ውስጥ በ4.90 በመቶ ጦር መሳርያዎችን በማስገባት ስድስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።