አሜሪካ ለሩስያ የጦር መሳርያ አምርተዋል ባለቻቸው የቻይና ኩባንያዎች ላይ የመጀመርያውን ማዕቀብ ጣለች
ዋሽንግተን በዩክሬን ጦርነት ቻይና ከፍተኛ የጦር መሳር ድጋፎችን እያደረገች ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ትከሳለች
ቤጂንግ ከሞስኮ ጋር ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ ግንኙነቶችን እያጠናከረች ቢሆንም በጦርነቱ ዙርያ ገለልተኝነቷን ትገልጻለች
አሜሪካ መቀመጫቸውን በቻይና ባደረጉ ሁለት ሰው አልባ አውሮፕላን አቅራቢዎች ላይ ማዕቀብ ጣለች።
ኩባንያዎቹ በሩስያ ከሚገኙ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን የሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮን) እና ሌሎች የጦር መሳርያዎችን ለሩስያ ጦር እንደሚያቀርቡ ተነግሯል፡፡
ማዕቀብ የተጣለባቸው አምራቾች ካለቀላቸው የጦር መሳርያዎች ባለፈ ቴክኖሎጂዎችን እና የጦር መሳርያ ክፍሎችን ለሩስያ አሳልፈው ይሰጣሉ ነው የተባሉ፡፡
በዩክሬን በሚደረገው ጦር ከፍተኛ የጦር መሳርያ ሽያጭ እና ድጋፎችን እንደምታደርግ በዋሽንግተን የምትከሰሰው ቻይና ወቀሳውን በተደጋጋሚ ስታስተባብል ተስተውላለች፡፡
የአሜሪካ ግምጃ ቤት አዲስ ይፋ ባደረገው ማዕቀቡ ኩባንያዎቹን በቀጥተኛ ወታደራዊ ድጋፍ ተጠያቂ አድርጓቸዋል፡፡
ግምጃ ቤቱ የቻይና ኩባንያዎች በሞስኮ "ጋርፒያ" የረጅም ርቀት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ለማምረት ከሩሲያ የመከላከያ ጦር መሳርያ አምራቾች ጋር ተባብረው እንደነበር በመግለጫው ገልጿል።
ሰው አልባ አውሮፕላኖቹ ወደ ሩሲያ ከመላካቸው በፊት በቻይና ዲዛይን ተደርገው እና ተሠርተው ለጦር ሜዳ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተደርገዋል ብሏል።
"ጋርፒያ" የተሰኝው በሁለቱ ሀገራ ጥምረት የተሰራው ድሮን የዩክሬን ግዝፍ መሰረተ ልማቶችን ለማውድም ጥቅም ላይ እንደዋለ ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
አሜሪካ ቀደም ሲል ለሩሲያ ወታደራዊ ኢንዱስትሪ መሠረት ወሳኝ ግብዓቶችን በሚያቀርቡ የቻይና ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጥላ የነበረ ቢሆንም፤ ከሩሲያ ኩባንያዎች ጋር በመተባበር የተሟላ የጦር መሣሪያ ስርዓቶችን በማዘጋጀት እና በማምረት ላይ በሚሳተፉ አምራቾች ላይ ማዕቀብ ለመጣል ስትወስን ግን ይህ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡
ማዕቀብ ከተጣለባቸው ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው “ያሚን ሊምባች” የተባለው የአውሮፕላኖች ሞተር አምራች ድርጅት በአሜሪካ የቀረበበት ክስ ሀሰተኛ መሆኑን እና ድሮኖችን ለሩስያ ልኮ እንዳማያውቅ አስተባብሏል፡፡
“ሬድሌፕስ ቪክተር ሼንዢን” የተባለው ኩባንያ ደግሞ ድሮኖቾን እና ሌሎች የጦር መሳርዎችን ለሩስያ በማድረስ ከሞስኮ ጦር መሳርያ አምራች ኩባንያዎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በመመስረት በማዕቀብ ዝርዝሩ ውስጥ ተካቷል፡፡
ቤጂንግ ከሁለት ዓመት ተኩል በላይ በፈጀው ግጭት ውስጥ ከሞስኮ ጋር ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ ግንኙነቶችን እያጠናከረች ቢሆንም በጦርነቱ ዙርያ ገለልተኝነቷን ትገልጻለች።
ቻይና ከፍተኛ ማዕቀብ ለተጣለባት ኢኮኖሚ ወሳኝ የህይወት መስመር በመስጠት የሩሲያ ከፍተኛ የንግድ አጋር ሆናለች፡፡
ከዚህ ባለፈም ሁለቱ የኒዩክሌር መሳሪያ የታጠቁ ወዳጅ ሀገራት በቅርብ ወራት ውስጥ የሚያደርጓቸውን የጋራ ወታደራዊ ልምምዶች አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡