በዋሽንግተን ግዛት 'የናሽናል ጋርድ' ወታደሮች በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ታዘዙ
ዲሞክሬቶች ትራምፕ የድምጽ ቆጠራው ሳይጠናቀቅ አሸንፌያለሁ ብለው ሊያውጁ ይችላሉ የሚል ስጋት አድሮባቸዋል
የዋሽንግተን ግዛት ገዥ ከምርጫ 2024 ጋር ተያይዞ ሁከት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን ተከትሎ 'የናሽናል ጋርድ' ወታደሮች በተጠንቀቅ እንዲቆሙ አድርገዋል
በዋሽንግተን ግዛት የአሜሪካ ልዩ ኃይል ወታደሮች በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ታዘዙ።
የአሜሪካዋ ዋሽንግተን ግዛት ገዥ ባለፈው አርብ እለት እንደተናገሩት ከምርጫ 2024 ጋር ተያይዞ ሁከት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል መረጃ እና ስጋት መኖሩን ተከትሎ የተወሰኑ 'የናሽናል ጋርድ' ወይም ብሔራዊ ዘብ ወታደሮች በተጠንቀቅ እንዲቆሙ አድርገዋል።
በህዝብ አስተያየት መሰረት የዲሞክራቷ እጩ ካማላ ሀሪስ የሪፐብሊካኑን እጩ ድናልድ ትራምፕን በቀላሉ ያሸነፉበታል የተባለው ይህ ግዛት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የምርጫ ኮሮጆ ከተቃጠሉባቸው መካከል አንዱ ነው።
"ከምርጫ 2024 ጋር በተያያዘ የሚነሱትን ጥቅል ወይም የተለዩ መረጃዎችን እና ስጋቶችን በተመለከተ፣ ምላሽ ለመስጠት በደንብ መዘጋጀታችንን ማረጋገጥ እፈልጋለሁ" ሲሉ ገዥው ጄይ ኢንስሌ አርብ እለት በጽረ-ገጻቸው ላይ በታተመ ጽሁፍ መግለጻቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ዲሞክሬቶች ትራምፕ የድምጽ ቆጠራው ሳይጠናቀቅ አሸንፌያለሁ ብለው ሊያውጁ ይችላሉ የሚል ስጋት አድሮባቸዋል።
ነገርን ትራምፕ እንደ ምርጫ 2020 ቆጠራው ሳይጠናቀቅ ማሸነፋቸውን ካወጁ ዲሞክራቶች የሚሰጡትን ምላሽ ማዘጋጀታቸውን እየገለጹ ነው።
ሀሪስ ስለዝግጅቱ በዝርዝር ባይናገሩም፣ ስድስት ዲሞክራቶች እና የሀሪስ የምርጫ ዘመቻ ባለስልጣናት ትራምፕ ቀድሞው አሸንፌያለሁ የሚሉ ከሆነ የመጀመሪያው ውጊያ በህዝብ ፊት ይሆናል ብለዋል።
ዲሞክራቶች እንደገለጹት አሸናፊነት ከመታወጁ በፊት ቆጠራው ይጠናቀቅ የሚሉ መልክቶችን በማህበራዊ ሚዲያ እና በቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለማጥለቅለቅ አቅደዋል።
አንድ ከፍተኛ የሀሪስ የምርጫ ቅስቀሳ ባለስልጣን ባለፈው አርብ እንዳሉት ከሆነ ትራም በሀሰት ማክሰኞ ምሽት አሸንፌያለሁ ብለው እንደሚያውጁ "በደንብ እጠብቃሉሁ" ብለዋል።
"ከዚህ በፊት አድርጎታል፤ ከሽፏል። ድጋሚ የሚያደርገው ከሆነ በድጋሚ ይከሽፋል"ብለዋል ባለስልጣኑ።
በ2020 ምርጫ ትራምፕ ማሸነፋቸውን ያወጁት ምርጫ ከተጀመረ ከሰአታት በኋላ ነበር። ነገርግን በመጨረሻ በጆ ባይደን ተሸንፈዋል። ትራምፕ እስካሁን ድረስ የምርጫውን ውጤት ያልተቀበሉ ሲሆን የተሸነፉት መጠነሰፊ በሆነ ማጭበርበር ድምጽ ተሰርቀው እንደሆነ ያምናሉ።
ትራምፕ የምርጫውን ውጤት እንማይቀበሉ መግለጻቸው ተከትለው ደጋፊዎቻቸው በ2021 በካቲቶል ሁከት ማስነሳታቸው ይታወሳል።