ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል፤ መቼስ ይጠናቀቃል?
ጠ/ሚ ዐቢይ የግድቡ የሲቭል ስራ እስክ ፊታችን ታህሳስ ወር ድረስ መቶ ፐርሰንት ይደርሳል ብለዋል
የግድቡ አብዛኛው ስራ በቀጣይ ታህሳስ ወር የመጨረሻው ምእራፍ ላይ ይደርሳል- ጠ/ሚ ዐቢይ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሲቪል ስራ እስክ ፊታችን ታህሳስ ወር ድረስ መቶ ፐርሰንት እንደሚደርስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በትናንትናው እለት ተጨማሪ ሁለት ተርባይኖች ወደ ኃይል ማምረት መግባታቸውን አስመልከቶ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ “የግድቡ አበብዛኛው ስራ በቀጣይ ታህሳስ ወር የመጨረሻው ምእራፍ ላይ ይደርሳል” ያሉ ሲሆን፤ አጠቃላይ የግድቡ ስራ ደግሞ የዛሬ ዓመት ገደማ ሙሉ በሙሉ የጠናቀቃል ብለዋል።
በታህሳስ ወር የግድቡ የሲቭል ስራ መቶ ፐርሰንት ይደርሳል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራም አብዛኛው እየተጠናቀቀ ነው፤ በቀጣይ 6 ወራት ሙሉ በሙሉ ወደ ማጠናቀቂያው ምእራፍ ይደርሳል ሲሉም ተናግረዋል።
ትናንት ስራ የጀመሩትን ሁለት ተርባይኖች ጨምሮ አሁን ላይ አራት ተርባይኖች ኃይል እያመረቱ ሲሆን፤ ከ4 ወራት በኋላ 3 ተጨማሪ ተርባይኖች ወደ ስራ እንደሚገቡ እና ኃይል የሚያመነጩ ተርባይኖች ቁጠር 7 እንደሚደርስም ገልጸዋል።
ከግድቡ ውሃ መያዝ ጋር በተያያዘም ግድቡ አሁን ላይ 62.5 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ መያዙን እና እስከ መጪው ታህሳስ ወር ከ70 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ ውኃ መያዝ እንደሚችልም ተናግረዋል።
አሁን ላይ ውሃ የተኛበት ቦታ 200 ኪሎ ሜትር በላይ መሸፈኑንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያስታወቁት።
የአባይ ወንዝ ፍሰት ሳይስተጓጎል ከመቀጠሉም በተጨማሪ የግድቡ የውሃ ማስተንፈሻ በሮች ተከፍተው በሰከንድ 2‚800 ሜትር ኪዩብ ተጨማሪ ውሃ ማፍሰስ መጀመራቸውንም አስታውቀዋል።
የህዳሴ ግድብ ሁለት ተጨማሪ ተርባይኖች ሥራ መጀመራቸውን በትናንትናው እለት መገለጹ ይታወሳል።
በትናንትናው እለት ሃይል ማመንጨት የጀመሩት ሁለቱ ተርባይኖች ግድቡ የሚያመነጫን የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን በሁለት እጥፍ የሚያሳድገው ይሆናል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለት ተርባይኖች በየካቲትእና ነሃሴ 2014 ዓ.ም ኃይል ማመንጨት መጀመራቸው ይታወሳል።
የካቲት ወር 2014 ዓ.ም ግድቡ ካሉት ተርባይኖች ውስጥ አንዱ የሆነው እና ዩኒት 10 የሚል መጠሪያ ያለው ተርባይን 270 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ይታወሳል።
ግድብ ካሉት 13 ተርባይኖች መካከል ዩኒት 9 የሚባለው ሁለተኛው ተርባይን ደግሞ በዚያው ዓመት ነሃሴ ወር ላይ ኃይል የማመንጨት ጀምሯል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከሰሞኑ የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸሙን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ኢትዮጵያ ካመረተችው የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ ሕዳሴ ግድብ 17 በመቶ ድርሻ መሸፈኑን አስታውቋል።