“120 ሚሊየን ህዝብ የምናስተዳድረው ከ64 ሺህ ግለሰቦችና ኩባንያዎች በምንሰበስበው ግብር ነው” - ጠ/ሚ ዐቢይ
ኢትዮጵያ ከአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ጋር የምታደርገው ድርድር ከተሳካ 10 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ታገኛለች ብለዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የውጭ እዳ ጫና ከጠቅላላ ሀገራዊ ምርት አንጻር በ17.5 በመቶ መቀነሱን ተናግረዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ እየሰጡ ነው።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ የፋይናንስ ሴክተር ፣ ግብርና፣ የገቢ እና ወጪ ምርት፣ የግብር አሰባሰብ እና ሌሎችም ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮችን ዳሰዋል።
የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ካጎበጡ መሰረታዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ የሆነውን የውጭ እዳ ጫና በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ባለፉት 6 አመታት 10 ቢሊየን ዶላር ለውጭ እዳ መከፈሉን አንስተዋል።
መንግስታቸው የእዳ ጫናን ለማቃለል ወስዶታል ባሉት እርምጃ ከጥቅል ሀገራዊ ምርቱ የነበረውን ድርሻ ወደ 17.5 በመቶ ማውረድ ተችሏል ነው ያሉት።
የግብር ገቢን በተመለከተ በበጀት አመቱ 529 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ በ11 ወራቱ 466 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉን ጠቅላይ ሚንስትሩ በምላሻቸው ተናግረዋል።
“ከ64 ሺህ ኩባንያዎች እና ግለሰቦች በምናገኝው ገቢ የ120 ሚሊየን ህዝብ ጥያቄ ለመፍታት እየሰራን ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ ከጠቅላላ ሀገራዊ ምርት አንጻር የምንሰበስበው ገቢ 7 በመቶ ብቻ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በቀጠናው ከሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት አንጻር የምትሰበስበው ታክስ ዝቅተኛ ነው መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ማሻሻል እንደሚገባ አንስተዋል።
መንግስት የበጀት ጉድለቱን ለመሙላት በገቢ አሰባሰብ ላይ ያሉ አሰራሮችን ማሻሻል ያስፈልጋል ያሉ ሲሆን፤ የታክስ ስወራ፣ ኮንትሮባንድ፣ የንግድ ማጭበርበር እና ሌሎችም ከገቢ ጋር የተገናኙ ክፈተቶች ከፍተኛ ተግዳሮቶች ናቸው ነው ያሉት።
በወጭ እና በገቢ ምርቶች መካከል ያለው የንግድ ልዩነት አሁንም ከፍተኛ እንደሆነ ይታወቃል ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ኢትዮጵያ በአመት ከ7 ቢሊየን ዶላር በላይ ለእዳ ክፍያ፣ ለአፈር ማዳበርያ እና ለነዳጅ ወጪ ታደርጋለች ብለዋል።
ሆኖም ሀገሪቱ ለውጭ ገበያ ከምታቀርባቸው ምርቶች የምታገኝው ገቢ 4 ቢሊየን ዶላር የማይሞላ ነው። በ11 ወራቱ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሆኑ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት መተካት ተችሏል።
ለአፈር ማዳበርያ እስከ 2 ቢሊየን ዶላር ወጪ እንደሚደረግ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚንስትሩ በአመት እስከ 15 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበርያ ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ ይገኛል ብለዋል።
በግብርናው ዘርፍ በ2015/16 የምርት ዘመን 507 ሚሊየን ኩንታል የግብርና ምርት የተመረተ ሲሆን ይህም ከባለፈው የምርት ዘመን 100 ሚሊየን ኩንታል ብልጫ እንዳለው ነው የተገለጸው።
ጠቅላይ ሚንስትሩ የኑሮ ውድነትን ለማቃለል በተወሰደ እርምጃ መንግስት 10 ቢሊየን ብር ገቢ ማጣቱን ገልጸው፤ በዚህም የዋጋ ንረቱን ባለፈው ዓመት ከነበረበት 30 በመቶ ወደ 23 በመቶ ዝቀ ማድረግ መቻሉን አመላክተዋል።
የፋይናንስ ሴክተሩን አስመልክቶ በሰጡት ምላሽ የውጭ ሀገራት ባንኮች በሀገር ውስጥ ገበያ የሚፈጥሩት ፉክክር እና የአሰራር መዘመን ታስቦበት በቅርቡ ገበያውን እንደሚቀላቀሉ አረጋግጠዋል።
በአሁኑ ወቅት 32 የሀገር ውስጥ ባንኮች የሚገኙ ሲሆን ለሚመጣው ውድድር ለመዘጋጀት አቅማቸውን ሰበሰብ አድርገው ቢወሀዱ አሰራራቸውንም ቢከልሱ ተጠቃሚ ይሆናሉ ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅት 100 ሚሊየን የቁጠባ ሂሳብ እንዳለ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስታቸው ስልጣን ከመያዙ በፊት ከነበረው የቁጠባ ሂሳብ ከእጥፍ በላይ መጨመሩን ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት ከ6 አመት በፊት ከነበረበት 86 ቢሊየን ዶላር ወደ 205 ቢሊየን ዶላር ከፍ ብሏል ፤ ዘንድሮ በኢኮኖሚ 7 ነጥብ 9 በመቶ እድገት እንደሚጠበቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው በሰጡት ማብራርያ አመላክተዋል፡፡
የውጭ ምንዛሪ ችግርን ለመቅረፍ እና መንግስት የጀመረውን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ ለማድረግ ከአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ጋር የሚደረገው ድርድር የቀጠለ ሲሆን ድርድሩ የሚሳካ ከሆነ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አመታት 10 ቢሊዮን ዶላር ከተቋሙ እንደምታገኝ አንስተዋል።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ስብሰባ የቀጠለ ሲሆን በቀሪ ቆይታው በወቅታዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጠቅላይ ሚንስትሩ ማብራርያ የሚሰጡ ሲሆን በመጨረሻም ምክር ቤቱ የ2017 በጀትን እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።