20 በመቶ ናይጀሪያዊያን ስራቸውን በኮቪድ ምክንያት አጥተዋል ተብሏል
ዓለም አቀፉ የገንዘብ አበዳሪ ተቋም ዓለም ባንክ ባወጣው መግለጫ በአፍሪካ ቀዳሚ የህዝብ ቁጥር ባለቤት ለሆነችው ናይጀሪያ ከኮሮና ቫይረስ ጉዳት እንድታገግም የሚረዳ 400 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጓል።
የገንዘብ ድጋፉን የባንኩ የቦርድ ዳይሬክተሮች ያጸደቁ ሲሆን የገንዘብ ድጋፉ ናይጀሪያ የኮሮና ቫይረስ ክትባት እንድትገዛ እና ሌሎች ስራዎችን እንድትከላከል ያስችላታል ተብሏል።
የናይጀሪያ መንግስት በበኩሉ ከዓለም ባንክ ባገኘው ድጋፍ 110 ሚሊዮን ዜጎችን መከተብ የሚያስችል የኮሮና ቫይረስ ክትባት እንደሚገዛበት መግለጹን ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል።
በናይጀሪያ 20 በመቶ የሚሆኑ ዜጎች ኮሮና ቫይረስ ባስከተለው ጉዳት ምክንያት ስራቸውን ያጡ ሲሆን ክትባቱን በፍጥነት ለዜጎች መስጠት ጉዳቱን እንደሚቀንስ ተገልጿል።
200 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ናይጀሪያ 5 ሚሊዮን ዜጎቿን የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት የሰጠች ሲሆን በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ 50 በመቶ ናይጀሪያዊያንን የመከተብ እቅድ እንዳላት የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የኮሮና ቫይረስ ከ205 ሺህ በላይ ናይጀሪያዊያንን ያጠቃ ሲሆን ከ2 ሺህ 700 በላይ ዜጎችን ደግሞ እንደገደለ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያስረዳል።
በዓለማችን በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ዜጎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ደግሞ 5 ሚሊዮንን ተሻግሯል።
አሜሪካ፤ሩሲያ እና ብራዚል ከዓለማችን ብዙ ዜጎቻቸው በኮቪድ ምክንያት የሞቱባቸው ሀገራት ሲሆኑ ደቡብ አፍሪካ፤ሞሮኮ እና ቱኒዝያ ደግሞ ከአፍሪካ ቀዳሚዎቹ ሀገራት ናቸው።