ግለሰቡ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች "እባካችሁ ሁላችሁም ጸልዩ" ሲልም ሆስፒታል ሆኖ የተነሳቸውን ፎቶግራች አጋርቷል
በማህበራዊ የትስስር ገጾች በኮቪድ -19 ክትባቶች ላይ ያሾፈ አንድ የካሊፎርኒያ ነዋሪ ለአንድ ወር ያህል ከቫይረሱ ጋር ሲታገል ቆይቶ ህይወቱ አልፏል።
የሂልሶንግ ሜጋች ቤተክርስቲያን አባል የሆነው ስቴፈን ሃርመን ክትባቱን ከመቃወም ባለፈ በክትባቱ ዙሪያ በተከታታይ ይቀልድ እንደነበርም ነው የአሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ የሚያመለክተው።
የ34 ዓመቱ ግለሰብ በሰኔ ወር 7 ሺህ ተከታዮች ባሉት የትዊተር ገጹ ላይ "99 ችግሮች ሲኖሩብኝ ክትባቱ ግን ከዚህ ውስጥ አይካተትም" ብሎ ነበር።
“የባይደን ቤት ለቤት ክትባት ኃሳብ ሰጪዎች ወይም አማካሪዎች የጃኮቪድ ምስክሮች/ JaCovid Witnesses/ መባል አለባቸው” በማለት ሲቀልድ እንደነበርም እንዲሁ የሚታወስ ነው።
በመጨረሻም በሳንባ ምች እና በኮቪድ-19 ምክንያት ከሎስ አንጀለስ ወጣ ባለ ሆስፒታል ህክምናውን ሲከታተል የቆየው ስቴፈን ሃርመን ረቡዕ ዕለት ህይወቱ ልያልፍ ችሏል።
ከመሞቱ በፊት በነበሩት ቀናት ውስጥ ሃርመን በሕይወት ለመኖር ያደረገውን ትግል በሆስፒታሉ አልጋው ላይ የተነሳቸውን ፎቶግራፎች በመለጠፍ አሳይቷል።
"እባካችሁ ሁላችሁም ጸልዩ ፣ እኔን ለመተንፈስ ባለመቻሌ በመተንፈሻ ማገዣ መሣሪያ ሊደግፉኝ ነው" ብሏል።
ሃርመን በረቡዕ ዕለት የመጨረሻ የትዊተር መልዕክቱ በመተንፈሻ መሣሪያ ድጋፍ ለመተንፈስ መወሰኑን አስታውቋል።
"መቼ እንደሆነ ባላውቅም እነቃለሁ፣ እባካችሁ ጸልዩ" ሲልም ጽፎ ነበረ።
ሃርመን ከቫይረሱ ጋር እየታገለም ቢሆንም እምነቴ ይጠብቀኛል በማለት ክትባቱን እንደማይቀበል ተናግሯል።
ከመሞቱ በፊት ስለወረርሽኙ እና ስለ ክትባቶቹ በመቀለድ ከአሜሪካን ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ ከሆኑት ከዶክተር አንቶንዮ ፋውቺ ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት አለኝ በማለት አስቂኝ ምስሎችን አካፍሏል።
የሂልሰንግ ቤተክርስቲያን መስራች ብሪያን ሂዩስተን ሐሙስ ዕለት በትዊተር ገጻቸው ህይወቱ ማለፉን አረጋግጠዋል።
ካሊፎርኒያ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የኮቪድ -19 ቁጥር እየጨመረ የመጣ ሲሆን ወደ ሆስፒታል ከተወሰዱት አብዛኛዎቹ ክትባት ያልወሰዱ መሆናቸው እየተነገረ ይገኛል።