እስከ 40 የሚደርሱ ሀገራት 2ኛ ዶዝ የኮቪድ 19 ክትባት ለዜጎቻው መስጠት ተስኗቸዋል- የዓለም ጤና ድርጅት
የክትባት እጥረቱ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት፣ ላቲን አሜሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራ ነው የተከሰተው
የህንዱ የአስትራዜኒካ አምራች ሴረም ኢንስቲትዩት ለሀገር ውስጥ ቅድሚያ በመስጠቱ ነው እጥረቱ የተከሰተው
ከ30 እስከ 40 የሚደርሱ ሀገራት የመጀመሪያውን የኮቪድ 19 ክትባት ዶዝ ለወሰዱ ዜጎቻው 2ኛ ዶዝ ክትባት መስጠት እንደተሳናቸው የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።
በተለይም አስትራ ዜኒካ ክትባትን የሚጠባበቁ ሀገራት 2ኛ ዶዝ ክትባቱን ለመከተብ እጥረት እንዳጋጠማቸው የዓለም ጤና ድርጅት የስራ ኃላፊዎች በትናትናው እለት ማሳወቃቸውን ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አማካሪ ብሩስ አልዋርድ፤ ብርካታ ቁጥር ያላቸው ሀገራት ሁለተኛውን ዙር ክትባት ለዜጎቻቸው መስጠት ለማቆም ተገደዋል ብለዋል።
በተለይም ክትባቱን ከህንዱ ሴረም ኢንስቲትዩት በዓለም ጤና ድርጅት በሚመራው የኮቫክስ ጥምረት አማካኝነት የሚከፋፈልላቸው ሀገራት አቅርቦት መጠን መቀነሱ ተነግሯል።
ምክንያቱም በህንድ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በክፍተኛ መሰራጨቱን እና ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ተከትሎ የህንዱ ሴረም ኢንስቲትዩት ለሀገር ውስጥ ቅድሚያ በመስጠቱ ነው ተብሏል።
አማካሪው ብሩስ አልዋርድ፤ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት፣ ላቲን አሜሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅ፣ እና እንደ ኔፓልና ስሪላንካ ያሉ የህንድ ጎረቤት ሀገራት የክትባት እጥረቱ እንዳጋጠማቸውም አስታውቀዋል።
በዓለም ጤና ድርጅት የክትባት ዲፓርትመንት ዳይሬክተር ካትሪን ኦብሪየን በበክላቸው፤ “ከእነዚህ ሀገራት አብዛኛዎቹ ያላቸው የክትባት ክምችት እያለቀ ነው” ብለዋል።
ደካማ የክትባት ስርዓት ያላቸው ሀገራት በክትባት ቁጥር መቀነስ ክፉኛ ይጎዳሉ ያሉ ሲሆን፤ በህዝቡ ዘንድ ያለውን በራስ መተማመን እንደሚጎዳም አንስተዋል።