ዩክሬን የምትተማመንበትን የጦር አውሮፕላን አብራሪ በአደጋ ምክንያት አጣች
በዩክሬን ዋና ከተማ ኬቭ አቅራቢያ ሶስት የጦር አውሮፕላን አብራሪዎች ህይወታቸው አልፏል
አሜሪካ በቅርቡ ኬቭ ኤፍ 16 የጦር ጄቶችን ከአውሮፓ ሀገራት እንድታገኝ ፈቅዳለች
ዩክሬን የምትተማመንበት የጦር አውሮፕላን አብራሪ በአደጋ ምክንያት ህይወቱ ማለፉ ተነገረ።
"ጁስ" በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው አብራሪ ዩክሬን በሩሲያ ላይ ልትወስደው ለምታስበው የተጠናከረ የመልሶ ማጥቃት የአየር ዘመቻ ወሳኝ ሰው ነበር ተብሏል።
እንደ ሲኤንኤን ዘገባ ዩክሬን "የኬቭ ጠባቂ" በሚል ያዋቀረችው የአየር ሀይል ቡድን አባል የነበረው "ጁስ" ከዋና ከተማዋ ኬቭ 140 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በተፈጠረ አደጋ ህይወቱ አልፏል።
አደጋው የተፈጠረው ሁለት ተለማማጅ የአየር ሀይል አባላት L-39 የተሰኘው የጦር አውሮፕላን በማብረር ላይ እያሉ በተፈጠረ ግጭት ነው ተብሏል።
በአደጋው ሶስቱም አብራሪዎች ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን የሀገሪቱ ምርመራ ቢሮ አደጋውን በመመርመር ላይ መሆኑን አስታውቋል።
የደረሰው የአውሮፕላን አደጋ እና እንደ "ጁስ" አይነት ዝነኛ አብራሪዎች ህይወት ማለፍ ለዩክሬን አየር ሃይል ከባድ ሃዘን ሆኗል።
ዩክሬን F-16 የተሰኘውን የጦር አውሮፕላን ከተለያዩ የኔቶ አባል ሀገራት በማሰባሰብ ላይ ስትሆን ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ድጋፉ በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜና አሜሪካ ለዩክሬን የምትሰጠውን አይነተ ብዙ ድጋፍ ቀስ በቀስ ልትቀንስ እንደምትችል አስታውቃለች፡፡
ይህን ተከትሎም የአውሮፓ ሀገራት አሜሪካ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ወደ ስምምነት እንድትመጣ ግፊት ልታደርግ ትችላለች የሚል ስጋት እንደገባቸው ተገልጿል፡፡
በተለይም በአሜሪካ በቀጣይ አመት የሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የዩክሬን ጉዳይ ላይ ተጽዕኖ ሊያደርግ ይችላል በሚል ተሰግቷል፡፡