አሜሪካ ዩክሬን ወደ ሰላም እንድትመጣ ግፊት ልታደርግ እንደምትችል ተገለጸ
የአውሮፓ ሀገራት፥ አሜሪካ በኬቭ ላይ ጫና ልትፈጥር ትችላለች የሚል ስጋት አድሮባቸዋል ተብሏል
አሜሪካ በ2024 ለዩክሬን የምትሰጠውን ድጋፍ እንደምትቀንስ አስታውቃለች
አሜሪካ ዩክሬን ወደ ሰላም እንድትመጣ ግፊት ልታደርግ እንደምትችል ተገለጸ።
ለአንድ ሳምንት ልዩ ዘመቻ በሚል የተጀመረው የዩክሬን ሩሲያ ጦርነት 550 ቀን አልፎታል።
ይህ ጦርነት በፍጥነት እንዲቋጭ እና ሩሲያ ጦሯን ከዩክሬን እንድታስወጣ በሚል በሞስኮ ላይ ከ12 ሺህ በላይ ማዕቀቦች ተጥለዋል።
ይሁንና አሁንም 20 በመቶ የዩክሬን ግዛት በሩሲያ ጦር እንደተያዘ ሲሆን ለዩክሬን የጦር መሳሪያ እና ገንዘብ ድጋፍ ስታደርግ የቆየችው አሜሪካ ቀስ በቀስ ድጋፏን ልትቀንስ እንደምትችል ተሰግቷል፡፡
ብሉምበርግ እንደዘገበው ከሆነ አሜሪካ ለዩክሬን የምትሰጠውን አይነተ ብዙ ድጋፍ ቀስ በቀስ ልትቀንስ እንደምትችል አስታውቃለች፡፡
የአውሮፓ ሀገራት ደግሞ አሜሪካ ዩክሬን ወደ ስምምነት እንድትመጣ ግፊት ልታደርግ ትችላለች የሚል ስጋት እንደገባቸው ተገልጿል፡፡
በተለይም በአሜሪካ በቀጣይ አመት የሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የዩክሬን ጉዳይ ላይ ተጽዕኖ ሊያደርግ እንደሚል ተገልጿል፡፡
ለዩክሬን የሚሰጠው እርዳታ እንዲቆም የሚፈልጉ አሜሪካዊያን ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለኬቭ የሚሰጡትን ድጋፍ እንዲቀንሱ ሊያደርጋቸው ይችላልም ነው የተባለው።
አሜሪካ ባለፉት 18 ወራት ውስጥ ባቻ 43 ቢሊዮን ዶላር ለዩክሬን በመስጠት ቀዳሚ ሀገር ስትሆን ተጨማሪ ገንዘብ እንዳትሰጥ የተለያዩ ጫናዎች መኖራቸው ተገልጿል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ዩክሬን የጀመረችው የመልሶ ማጥቃት የታሰበውን ያህል ድል ማስመዝገብ አለመቻሏ እና አሁንም ምዕራባዊያን ተጨማሪ የጦር መሳሪያ እንዲልኩላት እየወተወተች መሆኑ አሜሪካ ዩክሬንን ወደ ሰላም ስምምነት እንድትገባ ጫና እንድታደርግ ሊያስገድዳት ይችላል በሚል ተሰግቷል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት ዩክሬን የተወሰኑ ግዛቶቿን ለሩሲያ በመስጠት ወደ ስምምነት እንድትመጣ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የስራ ሃላፊ ምክረሃሳብ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ዩክሬን የኔቶ ሃላፊውን ሃሳብ ሉአላዊነትን ያላከበረ በሚል ውድቅ ማድረጓም አይዘነጋም።
በ2024 የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ እጩ የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ ምርጫውን ካሸነፉ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ እንደማይሰጡ እና ጉዳዩን በድርድር እንዲፈታ ግፊት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡