ቻይናውያን የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በመፈለግ ላይ ሲያተኩሩ የምዕራባውያን ግን በገንዘብ ላይ ብቻ ታጥረዋል- ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ
የቻይና ኩባንያዎች በኡጋንዳ ያላቸውን ኢንቨስትመንት መጨመሩንም ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ አስታወቀዋል
ምዕራባውያን ኩባንያዎች ለኡጋንዳ ኢንቨስትመንት ያላቸው እይታ ጭፍን መሆኑንም ተናግረዋል
በኡጋንዳ የቻይና የግል ኢንቨስትመንት እያደገ እንደሚገኝ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዮዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ አስታወቁ።
ከሮይተርስ ጋር ቆይታ ያደረጉት ፕሬዝዳንቱ፤ በሀገራቸው ያለው የቻይና ኢንቨስትመንት መጨመሩን ሲገልጹ በአንጻሩ ምዕራባውያን በኡጋንዳ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት ማጣታቸውን ተናግረዋል።
ከአውሮፓውያኑ 1986 ጀምሮ በኡጋንዳ በፕሬዝዳንትነት ላይ ያሉት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ሀገራቸው በግብርና፣ በማዳበሪያ ማምረት፣በማዕድንና በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ከቻይና የግል ኩባንያዎች ጋር ለመስራት ስምምነት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ምዕራባውያን ኩባያዎች በኡጋንዳ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ ምንም አይነት ፍላጎት እንደሌላቸው ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፤ የቻይና ኩባንያዎች ግን ወደ ሀገሪቱ በመምጣት ዕድሎችን እንደሚያዩም ተናግረዋል።
ቻይናውያን የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በመፈለግና በማንኳኳት ላይ ትኩረት ሲያደርጉ ምዕራባውያን ግን በገንዘብ ሙላት ብቻ መታጠራቸውን ተናግረዋል።
የቻይና የመንግስትና የግል ኩባንያዎች በአፍሪካ ኢንቨስትመንት እንዲጨምር እያደረገ መሆኑ በተደጋጋሚ ይጠቀሳል።
የቻይና ፕሬዝዳንት “ቤልት ኤንድ ሮድ” የተሰኘው እንቅስቃሴ የቻይናን ኃያልነት እያስጠበቀ መሆኑ በተደጋጋሚ ይነሳል።