የአየር ንብረት ለውጥ አለምን ወደ “ረሃብ ቀውስ” እየገፋ ነው - የአለም ምግብ ፕሮግራም
በ2022 ብቻ 56 ነጥብ 8 ሚሊየን ሰዎች ለምግብ ዋስትና ችግር ተጋልጠዋልም ብሏል ድርጅቱ
የኮፕ28 ጉባኤ በዱባይ ሲካሄድ የአየር ንብረት ለውጥ እያደረሰ ያለው ጉዳት በስፋት ይዳሰሳል ተብሏል
የአየር ንብረት ለውጥ አለምን ወደ “ረሃብ ቀውስ” እየገፋ ነው አለ የአለም ምግብ ፕሮግራም።
ከሶስት ቀናት በኋላ በዱባይ የሚጀመረው የአለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤም (ኮፕ28) የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ በሰው ልጆች የምግብ ዋስትና ላይ እያሳደረ ያለው ተጽዕኖ በስፋት እንዲመከርበት ነው ድርጅቱ ያሳሰበው።
ጉባኤው በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለረሃብ እየተጋለጡ ለሚገኙ ሰዎች የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ያመላክታል ተብሎ ይጠበቃል።
በ2022 ብቻ 56 ነጥብ 8 ሚሊየን ሰዎች ለምግብ ዋስትና ችግር ተጋልጠዋል የሚለው የአለም ምግብ ድርጅት፥ አብዛኞቹ ተጠቂ ሀገራት ግጭትና አለመረጋጋት ያደቀቃቸው መሆናቸውም ችግሩን ይበልጥ እንዳባባሰው ገልጿል።
የመንግስታቱ ድርጅት በዱባይ በሚካሄደው የኮፕ28 ጉባኤ የእርሻ፣ ምግብ ዋስትና እና አየር ንብረት አለማቀፍ ማዕቀፍ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
በአለም የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) የሚመራው ይህ አዲስ አለማቀፍ ጥምረት በአረብ ኤምሬትስ ድጋፍ ይደረግለታል ተብሏል።
አለማቀፍ ጥምረቱ የአየር ንብረት ለውጥ በምግብ እና ግብርና ዘርፎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ የተለያዩ ሃሳቦችን እንደሚያቀርብ ይጠበቃል።