አፍሪካ ህብረት፣ ተመድ ፣አውሮፓ፣አሜሪካ እና ኢጋድ ህወሓት ባወጣው መግለጫ ዙሪያ ምን አሉ?
አፍሪካ ህብረት “ተፋላሚ ወገኖች በአስቸኳይ ተኩስ ለማቆም እንዲሰሩና የፊት ለፊት ንግግር እንዲያካሄዱ” ጥሪ አቅርቧል
የኢትዮጵያ መንግስት ጦርነቱ በድጋሚ ከመቀስቀሱ በፊት ከህወሓት ጋር ያለቅደመ ሁኔታ በየትኛውም ቦታ እንደሚደራደር መግለጹ ይታወሳል
ህወሓት በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በሚካሄደው የሰላም ድርድር ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን ትናንት ባውጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ህወሓት አቶ ጌታቸው ረዳን እና ጀነራል ጻድቃን ገ/ትንሳኤን ያከተተ ተደራዳሪ ቡድን መሰየሙን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
ህወሐት ትናንት ማምሻው በትግራይ የውጭ ግንኙነት ጸ/ቤቱ በኩል ባወጣው መግለጫ ፤ የተሰየመው ተዳራዳሪ ቡድን ወደፊት በሚደረገው ድርድር “የትግራይን መንግስት” የሚወከል ስልጣን ተሰጥቶታለል ብሏል፡፡
ህወሓት የተሰየመው ተደራዳሪ ቡድን “ሳይዘገይ ወደ ድርድር እንደሚገባ”ም ጠቁሟል፡፡
የአፍሪካ ህብረት በትግራይ ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ "አያመጣም" ሲል የነበረው ህወሓት፤ በትናንትናው መግለጫው ግን በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በሚደረግ ድርድር ላይ እንደሚሳተፍ ገልጿል፡፡
ጦርነቱን በድርድር ለመፍታት ሲያደርግ የነበረው የአፍሪካ ህብረት የህወሓት መግለጫ በአወንታ እንደሚመለከው አስታውቋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ፤የትግራይ ክልል መንግስት ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና በአፍሪካ ህብረት በሚመራ የሰላም ሂደት ለመሳተፍ ፍቃደኝነት ማሳየቱን በበጎ እንደሚቀበሉት አስታውቀዋል፡፡
እርመጃው በኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን ጥሩ እድል የሚፈጥር ነው ያሉት ሙሳ ፋኪ፤ “ተፋላሚ ወገኖች በአስቸኳይ ተኩስ ለማቆም እንዲሰሩና በአፍሪካ ህብረት መሪነት የፊት ለፊት ንግግር እንዲያካሄዱ” ጥሪ አቅርበዋል።
ፊት ለፊት የሚደረገው ድርድር በሁለቱም ወገኖች ተቀባይነት ያላቸው “ዓለም አቀፍ አጋሮችን ያካተተ” እንደሚሆንም ፍንጭ ሰጥተዋል የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበሩ ሙሳ ፋኪ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ህወሓት በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በሚደረገው የሰላም ሂደት ላይ ለመሳተፍ ባሳየው ፍላጎት ደሰተኛ መሆኑን ገልጿል፡፡
የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ፤ ሁለቱም ወገኖች ይህንን የሰላም እድል በመጠቀም ግጭትን በማቆም ለውይይት እንዲመርጡ ጠይቀዋል።
ሁለቱም ወገኖች፤ “በቅን ልቦና እና ሳይዘገዩ በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን ሂደት በንቃት እንዲሳተፉና ውይይቱ እንዲካሄድ ምቹ ሁኔታዎችን እንዲፈጥሩ እናበረታታለን” ብለዋል ዋና ጸሃፊው፡፡
ተመድ በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን የሰላም ሂደት ለመደገፍ ያለውን ዝግጁነት በድጋሚ አረጋግጠዋል፡፡
የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭትን በተመለከተ ተደጋጋሚ መግለጫዎች ስያወጣ የነበረው አውሮፓ ህብረት በበኩሉ የትግራይ ክልል መንግስት ጦርነቱ ባስቸኳይ እንዲቆምና በአፍሪካ ህብረት በሚመራው የሰላም ሂደት ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን መግለጹ በበጎ እንደሚመለከተው ገልጿል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ምክትል ፕሬዝዳንት ጆሴፕ ቦሬል በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ “እድሉ ሁሉም ሊጠቀሙበት ይገባል” ብለዋል፡፡
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ባወጣው መግለጫ ውጊያ ለማቆምና ያልተፈቱ ጉዳዮችን በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን ማስታወቁን “እናበረታታለን” ያሉት ደግሞ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንቶኒ ብሊንከን ናቸው፡፡
“ኤርትራና ሌሎችም ግጭቱን ከማቀጣጠል ሊቆጠቡ ይገባል” ሲሉም አክለዋል፡፡
አሜሪካ የኢትዮጵያን አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ትደግፋለች ያሉት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ አሜሪካ ከሀገሪቱ ጋር ወደነበራት “ጠንካራ አጋርነት” መመለስ እንደምትሻ ም አስታውቀዋል።
ሌላው የትግራይ ክልል መንግስት ለውይይት ያወጣው መግለጫ ሚበረታታ መሆኑ የገለጸው ደግሞ፤ የኢትዮጵያ ሁኔታን በቅርበት ሲከታታል እንደነበር የገለጸው የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት /ኢጋድ/ ነው፡፡
የኢጋድ ዋና ጸሃፊው ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በግጭት ውስጥ ያሉት ኃይሎች በአፍሪካ ህብረት መሪነት ለሚደረግ የሰላም ንግግር ለመመለስ ባሳዩት ፈቃደኝነት መደሰታቸው ገልጸዋል፡፡
“ኢጋድ ሁለቱም ወገኖች ለተኩስ ማቆምና ለሽምግልና ያሳዩት ቁርጠኝነት ይቀበላል”ም ነውም ያሉት ዋና ጸሃፊው፡፡
በፌደራል መንግስቱ እና በህወሓት መካከል የነበረው ጦርነት ለወራት ጋብ ብሎ የነበረ ቢሆንም ጦርነቱ በድጋሚ ሊቀሰቀስ ችሏል፤ ጦርነቱን በመጀመር አንደኛቸው ሌላኛቸውን በመክሰስ ላይ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በድጋሚ ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በየትኛው ቦታ ከህወሓት ጋር እንደሚደራደር መግለጹም ይታወሳል፡፡
ህወሓትም በተመሳሳይ ለድርድር ዝግጁ መሆኑን ቢገልጽም ህወሓት በአፍሪካ ህብረት ላይ እምነት እንደሌላው ሲገልጽ ቆይቶ ነበር፡፡