ፑቲን፤ “የኒውክሌር ጣቢያ ጥቃት አስከፊ መዘዝ ያስከትላል” ሲሉ የፈንሳዩን ፕሬዝዳንት አስጠነቀቁ
ፕሬዝዳነቱ፤ ዩክሬን በዛፖሪዝሂያ ጣብያ የራዲዮ አክቲቭ ቁሳቁሶች ላይ ጥቃት ሰንዝራለች ሲሉ ከሰዋል
ፑቲን፤ ኪቭ በመሰረተ ልማቶች ላይ ለመታደረሰው ጥቃት “ምዕራባውያን ተጠያቂ” ናቸው ብለዋል
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ በሩሲያ ቁጥጥር ስር ባለው የዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የሚደርሰው ጥቃት “አስከፊ መዘዝ” ያስከትላል” ሲሉ የፈረንሳዩ አቻቸው ፕሬዝዳንት ማክሮንን አስጠነቀቁ።
ከኢማኑዌል ማክሮን ጋር የስልክ ቆይታ የነበራቸው ፑቲን፤ ዩክሬን በጣብያው የራዲዮአክቲቭ ቁሳቁሶች ላይ ጥቃት እንደሰነዘረች ተናግረዋል።
ዩክሬን በምስራቅ ዶንባስ ግዛት የሚገኙ ሲቪል መሰረተ ልማቶችን ኢላማ እያደረገች ነው ያሉት ፑቲን፤ ለዚህም ለኪቭ የጦር መሳሪያ ድጋፍ በማደረግ ግጭቱ እንዲባባስ በማድረግ ላይ ያሉት ምዕራባውያን ተጠያቂ ናቸው ሲሉ ከሰዋል።
ፑቲን፤ በአከባቢው የሚገኙ የሩሲያ ስፔሻሊስቶች የጣቢያውን ደህንነት ለማስጠበቅ የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰዱ እንደሆነና ሞስኮ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአቶሚክ ኤጀንሲ ጋር በተቋሙ ውስጥ ላሉት ችግሮች "ፖለቲካዊ ያልሆኑ" መፍትሄዎች ላይ ለመስማማት ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል ።
ሩሲያ ይህንን ትበል እንጂ ዩክሬን በተቃራኒው በኒውክሌር ጣቢያው አከባቢ ጥቃት እየሰነዘረች ያለችው ሞስኮ ናት በማለት ክስ ስታቀርብ መቆየቷ የሚታወስ ነው።
በዚህም ለጣቢያው ደህንነት ሲባል ፤ የዛፖሪዝያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ስራውን እንዲያቆም መደረጉን በትናንትነው እለት አስታውቃለች።
የዩክሬን ብሔራዊ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ኢጀንሲ(ኢነርጎአቶም) እንደገለጸው፤ የኒውክሌር ጣቢያው ስራው እንዲቆም የተደረገው የሩሲያ ኃይሎች ያደረሱትን ጥቃት ተከትሎ ነው።
ጥቃቱን ተከትሎ ቁጥር 6 የኃይል ዩኒት ከአውታረ መረቡ ያለው መስመር እንዲቋረጥ መደረጉ የገለጸው ኤጀንሲው፤ ባለው ሁኔታ በመስመሩ ላይ ተጨማሪ ጉዳት የመድረስ እድሉ ከፍተኛ መሆኑም አስታውቋል።
ዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ጣቢያ በጦርነቱ ምክንያት በአከባቢው ላይ መጠነ ሰፊ የተኩስ ልውጦች እየተካሄዱ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ፤ በጣቢያው ላይ ጥቃት ከደረሰ የጨረር አደጋ እንዳያስከትል በርካቶች ስጋታቸው ሲገልጹ ቆይተዋል።
በጦርነት ውስጥ የሚገኙትና እርስ በርስ የሚካሰሲት ሩሲያና ዩክሬን በጣቢያው ላይ የሚያደርሱት ጥቃት ከሀገራቱ በዘለለ ለተቀረው ዓለም ያልተፈለገ መዘዝ ይዞ እንዳይመጣም ተስግቷል።
በዚህም ሁኔታው ያሰጋው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ቀደም ሲል ባወጣው መግለጫ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያው አከባቢ ከጦር ነጻ እንዲሆን ጥሪ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
ሁለቱም አካላት የኃይል ጣቢያው አካባቢ ውጊያ እንዲያቆሙ መጠየቁም እንዲሁ አይዘነጋም።
አሜሪካም ብትሆን ቦታው ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ እንዲሆንና ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) ቦታውንና አከባቢው ከማንኛውም ወታደራዊ እንቅስቀሴ አሳስባ ነበር።
ደቡብ ምስራቅ ዩክሬን የሚገኘው ዛፖሪዝሂያ አቶሚክ ኃይል ማመንጫ በአውሮፓ ትልቁና በዓለም ላይ ካሉት 10 ትላልቅ የኒውክሌር ኃይል ጣቢያዎች መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል።