ብሪክስ በጉባኤው መጠናቀቂያ ላይ ስለ መካከለኛው ምስራቅ ቀውስ ምን አለ?
መሪዎቹ በጋራ የአቋም መግለጫቸው ፍልስጤም ራሷን የቻለች ሀገር ሆና እንድትመሰረት ጠይቀዋል
የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት የአለም አቀፍ ሰላምና ደህንነት ጠበቃ በመሆን የእዚህን ቀውስ እሳት ለማጥፋት አቅም የለውም በሚል ተወቅሷል
ሳለፍነው ማክሰኞ ጀምሮ በሩሲያ ካዛን ከተማ ሲካሄድ የነበረው 16ኛው የብሪክስ አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ በትላንትናው እለት ተጠናቋል፡፡
የዘንድሮው ጉባኤ ከምዕራባውያን ተጽዕኖ እና ማዕቀብ የተላቀቀ አማራጭ የፋይናንስ ስርአት መዘርጋት፣ በአባል ሀገራቱ መካከል የልማት ባንክ መቋቋም እና የመገበያያ ገንዘብን ማስተዋወቅ ላይ ትኩረቱን አድርጓል፡፡
ከዚህ ባለፈም የዩክሬን እና የጋዛ ጦርነት በጉባኤው ሰፊ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ምንም እንኳን የትኛውንም ግጭት ለማስቆም ሊጠቀስ የሚችል የመፍትሄ እርምጃ ባይቀርብም ተሳታፊዎቹ በሁለቱ ስፍራዎች እየተስፋፋ የመጣው ጦርነት መቆም እንደሚኖርበት እና ሰላማዊ መፍትሄዎች ወደ ፊት መምጣት እንደሚኖርባቸው አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡
የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ዢንፒንግ እና የህንዱ ናሪንድራ ሞዲ በዩክሬን እየተካሄደ የሚገኘው ጦርነት እልባት እንዲሰጠው ጠንካራ ሀሳብ ከሰነዘሩት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ቻይና ለዩክሬን ግጭት የፖለቲካ እልባት ትፈልጋለች ያሉት የቻይናው ፕሬዝዳንት ሁኔታውን ቀድሞ ለማርገብ እና ለፖለቲካ እልባት መንገዱን ለማመቻቸት ያግዛል በተባለው ቤጂንግ እና ብራዚል ያቀረቡት ሀሳብ ላይ መመካከር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የመካከለኛው ምስራቅን በተመለከተ በጋዛ ሁሉን አቀፍ የተኩስ አቁም እንዲኖር፣ በሊባኖስ እየተስፋፋ የሚገኝው ጦርነት እንዲቆም እና እስራኤል እና ፍልስጤም እራሳቸውን የቻሉ ሀገራት ሆነው የሚቆሙበት የሁለት ሀገር መፍትሄ (two-state solution) መመለስ አለበት ብለዋል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በእስራኤል እና ኢራን ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ መካከለኛው ምስራቅ ሁሉን አቀፍ ጦርነት አፋፍ ላይ እንደሚገኝ ለጉባኤው ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ፍልስጤማውያን የሀገርነት እውቅና እስካላገኙ ድረስ የታሪካዊ “ኢፍትሀዊነት ሸክም” ስለሚሰማቸው ቀጠናው በቋሚ ቀውስ ውስጥ እና በቀጣይ ግጭት ውስጥ ሊዘልቅ እንደሚችል ፑቲን አሳስበዋል
የአለም አቀፉን ማህበረሰብ እና አለም አቀፍ ተቋማትን በተለይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጋዛን ጦርነት ማስቆም ባለመቻሉ የወቀሱት የኢራኑ ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዢሽኪያን ዝምታው መቀጠል የለበትም ብለዋል፡፡
"የጦርነቱ ነበልባል በጋዛ ሰርጥ እና በሊባኖስ ከተሞች መቀጣጠሉን ቀጥሏል፤ አለም አቀፍ ተቋማት በተለይም የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት የአለም አቀፍ ሰላምና ደህንነት ጠበቃ በመሆን የዚህን ቀውስ እሳት ለማጥፋት አስፈላጊው ብቃት የላቸውም"ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
የብሪክስ መሪዎች በጋራ የአቋም መግለጫቸው ላይ በ1967 ዓ.ም በነበረው የድንበር ውሳኔ ሉዓላዊ እና ነጻ የሆነች ፍልስጤም በሀገርነት እንድትመሰረት ጥሪ አቅርበዋል።