የሩሲያ፣ የህንድ እና ቻይና መሪዎች በዩክሬን ጦርነት እና የብሪክስ አባል ለመሆን ጥያቄ ባቀረቡ ሀገራት ዙርያ መከሩ
ፕሬዝዳንት ፑቲን በዚህ ወቅት ሩስያ ከተቆጣጠረቻቸው የዩክሬን ምስራቃዊ ግዛቶች ለቆ መውጣት የማይታሰብ መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል
መሪዎቹ በተጨማሪም ብሪክስን ለመቀላቀል ጥያቄ ያቀረቡ 30 የሚጠጉ ሀገራትን አባልነት ዙርያ መክረዋል
ምዕራባውያን የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ከአለም ለማግለል የሞከሩትን ጥረት አክሽፏል የተባለውን የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ሩሲያ እያስተናገደች ትገኛለች፡፡
የቻይናው ሺ ጂንፒንግ፣ የህንዱ ናሬንድራ ሞዲ በዩክሬን ስላለው ጦርነት ከፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ተወያይተዋል፡፡
መሪዎቹ ከዩክሬን ጦርነት ባለፈ ብሪክስን ለማስፋት በሚደረገው ጥረት ስብስቡን ለመቀላቀል ጥያቄ ባቀረቡ 30 የሚጠጉ ሀገራት አባልነት ዙርያ መክረዋል፡፡
የህንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ሞዲ በዩክሬን ሰላም እንደሚያስፈልግ በይፋ ለፑቲን ነግረዋቸዋል፤ የቻይናው ሺ ዢንፒንግ በበኩላቸው በዩክሬን ስላለው ጦርነት ከክሬምሊን አለቃ ጋር በዝግ ተወያይተዋል።
የዩክሬንን አንድ አምስተኛ ግዛት ተቆጣጥራ የምትገኘው ሩሲያ በዶንባስ ክልል የዩክሬን አብዘሀኛው የድንጋይ ከሰል እና የብረት ማዕድን የሚወጣባቸውን ሉሀንስክ እና ዶኔስክ 80 በመቶ ግዛትን ጨምሮ የዛፓሮዚያ እና የኬሬሶን ክልልን 70 በመቶ ይዛለች፡፡
ፑቲን ከመሪዎቹ ጋር በነበራቸው ውይይት ወቅት አሁን የሩሲያ አካል ናቸው ያሏቸውን አራት የምስራቅ ዩክሬን ክልሎች ሞስኮ በአውሮፓ ላይ ያላትን የደህንነት ስጋት ማስጠበቂያ በመሆናቸው በምንም እንደማይለወጡ አቋማቸውን በይፋ አንጸባርቀዋል፡፡
የመጨረሻው የብሪክስ የአቋም መግለጫ ጦርነቱን ለማቆም ከቻይና እና ከብራዚል እንዲሁም ከሌሎች አባል ሀገራት የመጡ ሀሳቦችን እንደሚያካት ይጠበቃል፡፡
ሌላው መሪዎቹ የመከሩበት ጉዳይ የብሪክስን መስፋፋት የተመለከተ ነው፤ በአሁኑ ወቅት ቱርክ ፣ ባህሬን እና ኩዌትን ጨምሮ ሌሎች ጠንካራ እና አዳጊ ኢኮኖሚ ያላቸው 30 የሚጠጉ ሀገራት አባል ለመሆን ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ከሁለት አስርተ አመታት በፊት የምዕራባውያንን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ለመቋቋም አላማው አድርጎ የተመሰረተው ብሪክስ በአሁኑ ወቅት 45 በመቶ የአለምን ህዝብ ቁጥር እና 35 በመቶ የአለም ኢኮኖሚን የሚይዝ ስብስብ ሆኗል፡፡
ሆኖም የአለምኢኮኖሚ እና ጂኦፖለቲካዊ ሚዛንን ባስጠበቀ መልኩ ተጨማሪ አባል ሀገራትን በማካተት ዙርያ በቡድኑ ዘንድ ልዩነት አለ፡፡
ፑቲን ግሎባል ሳውዝ በመባል የሚታወቁትን አፍሪካ ፣ ላቲን አሜሪካ ፣ እስያ ፣ ካሪቢያን እና የምስራቁ ክፍል ሀገራት ከብሪክስ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ያላቸውን ፍላጎት ችላ ማለት ስህተት ነው ብለዋል።
በተመሳሳይ ጊዜ ሚዛንን መጠበቅ እና የቡድኑን ውጤታማነት መቀነስን መከላከል አስፈላጊ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከትላንትናው እለት ጀምሮ በሩስያ ካዛን መካሄድ በጀመረው 16ተኛው የብሪክስ ጉባኤ ላይ፤ የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ዢንፒንግ፣ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሪንድራ ሞዲ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ፣ የአረብ አምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን እና የኢራኑ ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዝሽኪያንን ጨምሮ ከ20 በላይ መሪዎች እየተካፈሉበት ይገኛል፡፡