በዘንድሮው የብሪክስ ጉባኤ ላይ ሩስያ ማጉላት የምትፈልጋቸው ሀሳቦች ምንድን ናቸው?
የአለምን አንድ ሶስተኛ ኢኮኖሚ የሚሸፍኑ ሀገራት መሪዎች የሚሳተፉበት ጉባኤ በቀጣዩ ሳምንት ይካሄዳል
ሞስኮ ከምዕራባውያን ተጽዕኖ የተላቀቁ አማራጭ የገንዘብ ተቋማትን መገንባት እንደሚያስፈልግ እየገለጸች ነው
ሩስያ በሚቀጥለው ሳምንት በሚካሄደው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የምዕራባውያን ተጽዕኖን መቀነስ የሚያስችሉ አጀንዳዎችን ማጉላት እንደምትፈልግ ተነገረ፡፡
ሀገሪቱ ከምዕራባውያን ማዕቀብ ነፃ የሆነ የአለም አቀፍ ክፍያ አማራጭ ስርአት እንዲገነባ የብሪክስ ሃገራትን ለማሳመን ትፈልጋለች ተብሏል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ አራት ሀገራትን በአዲስ አባልነት የተቀበለው የብሪክስ አባል ሀገራት ስብስብ የአለምን አንድ ሶስተኛ ኢኮኖሚ የሚያንቀሳቅስ ነው፡፡
በምዕራቡ አለም የሚመራውን የንግድ ስርአት እና ጂኦፖለቲካዊ ጉዳዮች የመገዳደር አላማ እንዳለው የሚነገርለት ስብስብ ከመጪው ማክሰኞ ጀምሮ በሩስያዋ ካዛን ከተማ ለ3 ቀናት ይካሄዳል፡፡
የሩሲያ የገንዘብ ሚኒስቴር እና ማዕከላዊ ባንክ አዘጋጅተውት ከጉባኤው ቀደም ብሎ ለጋዜጠኞች በተሰራጨው ሰነድ መሰረት፤ የብሪክስ ማዕከላዊ ባንኮችን እርስ በርስ በማያያዝ ክፍያ እንዲፈጸም የሚያስችል አዲስ የክፍያ ስርዓት በጉባኤው ላይ እንደሚተዋወቅ ይጠበቃል፡፡
ይህ የክፍያ ስርአት በሀገራቱ ገንዘብ የሚደገፍ እና በዲጂታል የክፍያ ስርአት ውስጥ የሚካተት ሲሆን በአባል ሀገራቱ መካከል ዶላር ሳያስፈልግ ግብይት እና ክፍያ እንዲፈጸም የሚያስችል ስለመሆኑ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ከዩክሬን ጋር የገባችበትን ጦርነት ተከትሎ በገንዘብ ዝውውር ስርአቶቿ ላይ የተለያዩ ማዕቀቦች የተጣሉባት ሩስያ፥ ቻይናን የመሳሰሉ ወዳጅ በምትላቸው ሀገራት ውስጥ ጭምር የሚገኙ ባንኮች ከአሜሪካ የሚመጣ ማዕቀብን ፍራቻ ግብይት ለመፈጸም ወደ ኋላ እያሉ ይገኛሉ፡፡
እንደ አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ )ያሉ ድርጅቶች የምዕራባውያን ሀገራትን ጥቅም እያስፈፀሙ ነው ሲሉ የሚከሱት የሩሲያ የገንዘብ ሚኒስትር አንቶን ሲሉአኖቭ፤ እየተሻሻለ ያለውን የአለም ኢኮኖሚ የበለጠ ለማገልገል ማሻሻያ እንደሚያስፈልግ የብሪክስ አባላትም ከአይኤምኤፍ የተሻለ ሌላ አማራጭ እንዲፈጥሩ ጠይቀዋል።
ሩሲያ ንግድን እና ኢንቨስትመንትን ለማሳለጥ "ብሪክስ ክሊር" የተባለ አሰራር ለመፍጠር ሀሳብ አቅርባለች።
ሰነዱ በአባል ሀገራት ውስጥ ባሉ የብድር ደረጃ ሰጪ ኤጀንሲዎች መካከል የተሻለ ግንኙነት እንዲኖር እና የጋራ የደረጃ አሰጣጥ ዘዴን የሚጠይቅ እንዲሁም እርስበርስ ያለውን የፋይናንስ ድጋፍ ለማሳደግ አላማው ያደረገ ነው፡፡
በዘንድሮው ጉባኤ ሁሉም የአባል ሀገራቱ መሪዎች እና በአጋርነት መስራት የሚፈልጉ ከ15 ሀገራት የተውጣጡ መሪዎች ይታደሙበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአሁኑ ወቅት ስብስቡን ለመቀላቀል ከ32 በላይ ሀገራት ጥያቄ ማቅረባቸውን ከሞስኮ የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡