ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ይረዳል ያሉት መፍትሄ ምንድነው?
“የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ባልነው ጊዜ እንደምናጠናቅቅ ሙሉ እምነት አለኝ”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በወጪ ንግድ እና በፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ ከፍተኛ እድገት ታይቷል ብለዋል
መንግስት በመጪው ዓመት የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ የኑሮ ውድነትን ለማቃለል እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ይህንን ያሉት ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራርያ ነው፡፡ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ከኢኮኖሚ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ለምክር ቤቱ አባለት በሰጡት ማብራሪያ፤ በበጀት ዓመቱ የኮቪድ-19፣ አንበጣ፣ የጎርፍ አደጋ፣ ሕይወት እና ንብረት የቀጠፉ ግጭቶችን በኢኮኖሚው ላይ ጫና መፍጠራቸውን አንስተዋል።
መጠናቀቅ ኖሮባቸው ያልተጠናቀቁ በርካታ ፕሮጀክቶችም ዕዳ ሆነው ወደዚህ በመሸጋገራቸው እንዲሁም፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበረ የዋጋ ግሽበት ወደ ኢትዮጵያ ኢምፖርት መደረገኑንም እንዲሁ ለኢኮኖሚው ፈታኝ እንደነበረ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስተሩ ሀገሪቱ በመሰል ፈተናዎች ብትታጀብም በእድገት ላይ ነበረች ያሉ ሲሆን፤ በተለያዩ ዘርፎች የተመዘገቡ ስከቶች እንደ አብነት አንስተዋል።
በ2011 ዓ.ም 9 በመቶ፣ በ2012 ዓ.ም.ኮቪድ እያለ 6 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት መገኘቱን በማስታወስ፤ በዚህኛው ዓመትም ከቡና እና ማዕድን የተገኘ ገቢ መገኘቱን ተከትሎ ከ2012 የተሻለ እና ለ2011 የቀረበ ዕድገት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በዛሬው እለት የስልጣን ዘመኑን የመጨረሻ ስብሰባ ያካሄደ ሲሆን ለ2014ዓ.ም በጀት አመት 561.67 ቢሊየን ብር እንዲሆን አጽድቋል፡፡ ከአጠቃላይ በጀቱ 200.9 ቢሊየን ብር ለክልሎች በድጎማ መልክ ይከፋፈላል ተብሏል፡፡
የአኮኖሚ እድገት
በወጪ ንግድ፣ የፋይናንስ እድገት እና የፕሮጀክቶች አፍጻጸሞች ላይ ከፍተኛ እድገት መታየቱን ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ ተናግረዋል፡፡
“ጠቅላላ የሀገር ውስጥ የምርት መጠን 100 ቢልዮን ዶላር /4.2 ትሪልዮን ብር/ ዘሏል” ያሉ ሲሆን፤ በባንኮች የሚዘዋወረው የገንዘብ መጠን 1 ትሪልዮን እንዲሁም የባንኮች አጠቃላይ ሀብትም 1.9 ትሪልየን ደርሷል” ነው ያሉት።
በገቢ እና ወጪ ያለው የንግድ ሚዛን ያለው ልዩነት ከ14.3 ሚልዮን ወደ 9.1 ሚልዮን ቀንሶ እየጠበበ መምጣቱን ያነሱ ሲሆን፤ የወጪ ንግድ መጠን 18 በመቶ መጨመሩ መድረሱንም አስታውቀዋል።
በዚህም በዘንድሮ በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከወጪ ንግድ 3 ነጥብ 5 ቢልየን ዶላር ማግኘቷንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል።
በቀጣይ ወጪ ንግድን በ2 በመቶ በማሳደግ የገቢ ንግዱን መጠንን በመግታት እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
የሀገሪቱ የዕዳ ጫና ከነበረበት 37 በመቶ ወደ 26 በመቶ ዝቅ ማለቱን ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ይህም ከወዳጅ ሀገራት ጋር በእዳ ማስተካከያ ላይ በመሰራቱ፣ ኮሜርሻል ብድሮች መቆማቸው እና በተወሰነ መልኩ እዳ ለመክፈል በመሞከሩ ነው ብለዋል።
“የውጭ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ የ20 በመቶ እድገት ተመዝግቧል፤ 2.7 ቢልየን ዶላር ወደ በገንዘብ እና በአይነት ለብሄራዊ ባንክ ገቢ መደረጉንም አስታውቀዋል።
የፋይናንስ ዘርፉን በተመለከተ ከፍተኛ የሆነ እድገት መታየቱን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ ከ2 ዓመት በፊት የነበረውን 38.8 ሚልየን የነበረው የባንክ ደንበኞች ቁጥር አሁን ላይ 66.2 ሚልየን መድረሱን እንደ ማሳያ አንስቷል፡፡
የባንክ ቅርንጫፎች ማደጋቸውንና የሞባይል ባንኪንግ ከተጀመረ ወዲህ 6 ሚልዮን ሰዎች ተጠቃሚ መሆናቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማሳያነትም አንስተዋል።
ኑሮ ውድነት
የግሽበቱ መንስኤዎች ውስጥ ዋነኛው አቅርቦት እና ፍላጎት አለመጣጣም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ሳንካዎች፣ ወደ ገበያው የሚለቀቀው ገንዘብ ቁጥጥር እና ክትትል፣ ከውጭ የሚገባ (ኢምፖርት) የሚደረግ የኑሮ ውድነት፣ ምርትን መያዝ እና መደበቅ ለግሽበት መንስኤዎች ናቸው ብለዋል።
መንግስት የኑሮ ውድነትን ለመግታት በዋና ዋና ሸቀጦች ላይ ድጎማ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎች ሲወስድ ቆይቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ አሁንም ቢሆን ልማትን በማፋጠን፣ የህዝብን ገቢ እና ምርትን በማሳደግ የኑሮ ውድነትን ለማቃለል የሚሰራ መሆኑንም ተቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒሰትሩ “የኑሮ ውድነት ለመቀነስ በተመረጡ ሸቀጦች ላይ ከሚያደርገው ድጎማ በተጨማሪ ህብርት ስራ ማህበራት የሚያከፋፍሉበት ሁኔት በማመቻቸት፣ የገበያ ማእከላት እንዲኖሩ በማድረግ እንዲሁም የግሉ ዘርፍ ተጨማሪ ታክስ ሳይከፍል ስነዴ፣ዘይትና ምርት እንዲያስገባ በመፍቀድ እየሰራ ነው” ብሏል፡፡
ምርት ማሳደግ በተለይም የበጋ ስነዴ ምርት ማሳደግ፣ በኩታ ገጠም የተጀመረው ስራ ማሳደግ፣ የግብርናው ዘርፍ በፋይናንስ ማገዝ እንዲሁም ዛፍ መትከል በቀጣይ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራባቸው ጉዳዮች መሆናቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግሯል፡፡
ህዳሴ ግድብ
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ዓላማ የኢትዮጵያን የመብራትና ኢኮኖሚ ጥያቄ መመለስ እንደሆነ ግልጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማብራሪያቸው አንስተዋል።
ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ጥያቄ ከመመለስ በዘለለ የግብፅን እና ሱዳንን ስጋት የሚቀንስ የዓለም ሀገራት በመገንዘብ ከህዳሴው ጋር ተያይዘው በሚነሱ ጉዳዮች ላይ አውንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ጠይቋል።
“የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ባልነው ጊዜ እንደምናጠናቅቅ ሙሉ እምነት አለኝ” ሲሉመ ተናግረዋል።