“የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2014 በጀት ዓመት በ8 ነጥብ 7 በመቶ እድገት እንደሚያስመዘግብ ይጠበቃል”- አቶ አህመድ ሺዴ
በ2014 በጀት ዓመት የዋጋ ግሽበቱ ወደ ነጠላ አሃዝ ይወርዳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል
የ2014 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት 561.7 ቢሊየን ብር እንዲሆን ለምክር ቤቱ ቀርቧል
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2014 በጀት ዓመት የ8 ነጥብ 7 በመቶ እድገት ሊያስመዘግብ እንደሚችል መተንበዩን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ አስታወቁ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው እለት በቀረበለት የ2014 ረቂቅ በጀት ላይ ውይይት አድርጓል።
በውይይቱ ላይ ተገኝተው ገለጻ ያደረጉት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከ2008 በጀት ዓመት ጀምሮ ተቀዛቅዞ መቆየቱን እና በርካታ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ ማለፉን ገልጸዋል።
ከ2012 በጀት ዓመት ጀምሮ የኢኮኖሚ እድገቱ ማንሰራራት መጀመሩን ያነሱት አቶ አህመድ፤ በበጀት ዓመቱ የ6 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ማስመዝገብ እንደተቻለም አስታውቀዋል።
በዚሁ በ2012 በጀት ዓመት የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ 1 ሺህ 80 የአሜሪካ ዶላር ድደረስ መቻሉን እና ይህም የሀገሪቱ መንግስት እና ህዝብ በጋራ በሰሩት ስራ የተመዘገበ መሆኑን አንስተዋል።
በከፍተኛ የሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈ የሚገኘው የ2013 በጀት ዓመት የኢኮኖሚ እድገት 8 ነጥብ 5 በመቶ ሆኖ እንደሚመዘገብ መተንበዩንም ሚኒስትሩ አንስተዋል።
በበጀት ዓመቱ በ9 ወራት ብቻ ከወጪ ንግድ ከ2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ መሰብሰቡን እና ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ21 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ጠቅሰዋል።
ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት የተሻለ እድገት እንደሚያስመዘግብ አመላካቾች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
"በዚህም የአጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገቱ 8 ነጥብ 7 በመቶ እንደሚሆን የተተነበየ ሲሆን የዋጋ ግሽበቱም ወደ ነጠላ አሃዝ እንደሚወርድ ይጠበቃል" ብለዋል።
ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ አክለውም ለምክር ቤቱ በቀረበው የ2014 የፌደራል መንግስት በጀት ላይ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ በዚህም የ2014 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት 561.7 ቢሊየን ብር እንዲሆን መቅረቡን አስታውቀዋል።
በጀቱ ለመደበኛ ወጪዎች ብር 162 ቢሊየን ብር፣ ለካፒታል ወጪዎች ብር 183.5 ቢሊዮን ብር፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ 203.95 ቢሊዮን ብር፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ 12 ቢሊዮን ብር ፣ በጠቅላላ ድምር ብር 561.67 ቢሊዮን በጀት በረቂቅ አዋጅ ተደግፎ ቀርቧል።
በረቂቅ በጀቱ ላይ የተወያው ምክር ቤቱም ለዝርዝር እይታ ለገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።