በነገው ዕለት ከሚጀምረው ከቻይና - አፍሪካ ትብብር ጉባኤ ምን ይጠበቃል?
ለ9ኛ ጊዜ የሚካሄደውን ጉባኤ ለመታደም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ወደ ቤጂንግ አቅንተዋል
በቻይና እና አፍሪካ መካከል ያለውን የንግድ ሚዛን ለማጥበብ ሀገሪቷ 300 ቢሊየን ዋጋ ያላቸው ምርቶችን ከአፍሪካ እንድትገዛ መሪዎች ጫና ያሳድራሉ ተብሎ ይጠበቃል
በነገው ዕለት ከሚጀምረው ከቻይና - አፍሪካ ትብብር ጉባኤ ምን ይጠበቃል?
የቻይና -አፍሪካ ትብብር ጉባኤ በነገው እለት መካሄድ ሲጀምር የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ወደ ቤጂንግ እያቀኑ ይገኛሉ፡፡
ከ50 በላይ ሀገራት መሪዎች የሚሳተፉበት ጉባኤ በዛሬው እለት ምሽት ላይ ከሚደረገው ፕሬዝዳንታዊ የእራት ግብዣ በኋላ በነገው እለት የተለያዩ የትብብር ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጎ መካሄድ የሚጀምር ይሆናል፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይ የሚፈረሙ ማዕቀፎች እስከ 2027 ድረስ የሚሰጡ የብድር እና የልማት ትብብሮችን እንደሚያካትቱ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ከ7 አመታት ወዲህ ቻይና ለአፍሪካ ሀገራት የምትሰጠው ብድር ከፍተኛ ጭማሪ ስለማሳያቱ ከሰሞኑ የወጡ የጥናት ውጤቶች ማመላከታቸው ይታወሳል፡፡
ባለፈው የፈረንጆቹ 2023 አመት ቤጂንግ ለአህጉሪቱ 4.61 ቢሊየን ዶላር ብድር ሰጥታለች፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይ ምን አዳዲስ ነገሮች ይጠበቃሉ በሚል ሰፊ ሀተታ ያወጣው ሮይተርስ ከአውሮፓ ሀገራት ጋር በታሪፍ ጭማሪ ውዝግብ ውስጥ የምትገኝው ቤጂንግ የአፍሪካ ሀገራት ተጨማሪ ምርቶችን እንዲገበዩ እንደምታግባባ ይጠበቃል ብሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በ2021 በተደረገው ጉባኤ ላይ የቻይናው ፕሬዝደንት ሺ ዢንፒንግ አፍሪካን ለማገናኘት የሚያግዙ 10 የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለማገዝ ቃል የገቡትን የድጋፍ አፈጻጸም የሚገመገም ይሆናል፡፡
ቻይና ከምዕራባውያን ሀገራት እና ከአሜሪካ ጋር ፉክክር ውስጥ የምትገኝበት የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ እና የታዳሽ ሀይል አማራጮችን ማስፋት ላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ሽያጭ ጨምሮ በሌሎች የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ሂደቶች ላይ ይመክራሉ፡፡
ዲጂታል ፋይናንስ ፣ የኦላይን ግብይት እና የአፍሪካ ማዕከላዊ ባንኮችን አቅም ማጠናከር ላይ ሀገራቱ እንደሚገኙበት ወቅታዊ ሁኔታ የተለያዩ ስምምነቶች ይፈረማሉ፡፡
የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ከቻይና የሚፈልጉት ምንድን ነው?
በከፍተኛ የውጭ እዳ ጫና ውስጥ የሚገኙት አብዘሀኞቹ የአህጉሪቷ ሀገራት አፋጣኝ የፋይናንስ መፍትሄን ይሻሉ፡፡ ይህም ከ2025-2027 ድረስ በሚተገበረው በዘንድሮው ጉባኤ በሚጸድቀው ማዕቀፍ ውስጥ እንዲካተት ፍላጎት አላቸው፡፡
እንደ ደቡብ አፍሪካ ያሉ ሀገራት ደግሞ ከቻይና ጋር ያላቸው ወጪ እና ገቢ ንግድ እንዲመጣጠን አልያም ልዩነቱ እንዲጠብ ጠይቀዋል፡፡
ቤጂንግ በዚህ ረገድ ሀገራቱ የሚያመርቱትን የግብርና እና የተፈጥሮ ማዕድናት ምርት መዳረሻ እንድትሆን የተለያዩ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ፍላጎታቸውን አንጸባርቀዋል፡፡
በዚህ መሰረትም በ2021 ጉባኤ ላይ ቃል በተገባው መሰረት ቻይና 300 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ያለው የአፍሪካ ሀገራትን ምርት እንድትገዛ የሚጠይቁ ይሆናል፡፡
ከ50 በላይ ሀገራት መሪዎች የሚሳተፉበት ጉባኤ አርብ የሚጠናቀቅ ሲሆን ጎን ለጎን የተለያዩ የሁለትዮሽ ውይይቶች የሚካሄዱበትም ይሆናል፡፡
ከትላንት ጀምሮ መሪዎች ጉባኤውን ለመታደም ወደ ቤጂንግ እያቀኑ ነው የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድም ወደ ስፍራው ተጉዘዋል፡፡