ቻይና ጋብቻን ቀላል ትዳርን መፍታት ግን የሚያከብድ ፖሊሲ አዘጋጀች
የህዝብ ቁጥር መቀነስ ያሳሰባት ቻይና ዜጎቿ እንዲጋቡ እና እንዲወልዱ የሚያበረታታ አሰራሮችን በመዘርጋት ላይ ናት
በቻይና ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የተጋቢዎች ቁጥር በ500 ሺህ ቀንሷል
ቻይና ጋብቻን ቀላል ትዳርን መፍታት ግን የሚያከብድ ፖሊሲ አዘጋጀች።
ለበርካታ ዓመታት የዓለማችን ቀዳሚ የህዝብ ቁጥር የነበራት ቻይና አዲስ የሚወለዱ ህጻናት እየቀነሱ ነው።
አሁን ላይ በዓለም ህዝብ ብዛት ሁለተኛዋ ሀገር የሆነችው ቻይና የህዝብ ቁጥሯን ለማሳደግ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በመዘርጋት ላይ ናት።
ለአብነትም አዲስ ለሚጋቡ ጥንዶች እና ልጆችን ለሚወልዱ ወላጆች ልዩ ማበረታቻዎችን ዘርግታለች።
አሁን ደግሞ ቻይናዊያን በቀላሉ እንዲጋቡ የሚፈቅዱ ህጎችን እና ትዳርን በቀላሉ ሙፍታት እንዳይቻል የሚያደርግ አዲስ ህግ ማርቀቋ ተሰምቷል።
እንደ ግሎባል ታየምስ ዘገባ ከሆነ ከዚህ በፊት ቻይናዊያን ጋብቻ ለመመስረት የግድ በትውልድ ቦታቸው መፈጸም ያለባቸው ቢሆንም ይህ አሰራር አሁን ዜጎች በፈለጉበት ቦታ ጋብቻ መፈጸም እንዲችሉ ይፈቅዳል።
እንዲሁም በትዳር ውስጥ ሆነው ልጆችን ለሚወልዱ ወላጆች የትምህርት ፣ ጤና እና ሌሎች ልዩ ድጋፎችን ማግኘት ያስችላቸዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ ግን ባለ ትዳሮች ፍቺ ለመፈጸም ከፈለጉ ብዙ አሰራሮችን እንዲከተሉ የሚያደርግ አዲስ ረቂቅ ህግ ተዘጋጅቷል ተብሏል።
ትዳሩን ለመፍታት ያመለከተ አንድ ሰው ማመልከቻውን ካስገባ በ30 ቀናት ውስጥ ማመልከቻውን መሰረዝ እንዲችል ይፈቅዳል።
በቻይና በኢኮኖሚ ጫናዎች ምክንያት የአዲስ ተጋቢዎች ቁጥር እየቀነሰ ሲሆን ለአብነትም ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የተጋቡ ቻይናዊያን ቁጥር ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር 500 ሺህ ገደማ ቅናሽ አሳይቷል።
እንደ ተመድ ስነ ህዝብ መረጃ ከሆነ ሕንድ 1 ነጥብ 44 ቢሊዮን ህዝብ በመያዝ የዓለማችን ቁጥር አንድ ሀገር ስትሆን ቻይና ደግሞ 1 ነጥብ 42 ቢሊዮን ህዝብ ብዛት አላት።