የወደፊቱ አጓጊ የስራ ዘርፎች የትኞቹ ናቸው?
የዓለም ኢኮኖሚ ጉባኤ የቀጣይ ዘመን ተፈላጊ ሙያዎችን ይፋ አድርጓል
ድርጅቱ በጊዜ ሂደት የሚጠፉ የሙያ መስኮችንም በጥናቱ ላይ ዘርዝሯል
የወደፊቱ አጓጊ የስራ ዘርፎች የትኞቹ ናቸው?
በየጊዜው እየዘመኑ የመጡት ቴክኖሎጂዎች የሰዎችን ህይወት በማቅለል ላይ ናቸው።
በተለይም የአርቲፊሺያል ኢንተለጀንስ ፈጠራዎች እየተራቀቁ መምጣታቸውን ተከትሎ አዳዲስ ስራዎች እየተፈጠሩ ሲሆን በቴክኖሎጂ ምክንያት ደግሞ ከገበያ ውጪ የሚሆኑ ስራዎችም አሉ።
የዓለምን ኢኮኖሚ በሚመለከት ጥናቶችን እና ውይይቶችን በማዘጋጀት የሚታወቀው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም በቀጣይ ተፈላጊ የስራ አይነቶችን በጥናቱ ይፋ አድርጓል ሲል ዩሮ ኒውስ ዘግቧል።
በጥናቱ መሰረትም በቀጣይ እጅግ ተፈላጊ የሚሆነው የሙያ ዘርፍ የመጀመሪያው የማሽን ለርኒንግ ስፔሻሊስት ሲሆን የዘላቂነት ስፔሻሊስት ደግሞ ሁለተኛው ተፈላጊ ሙያ ይሆናል ተብሏል።
የቢዝነስ ኢንተለጀንስ ተንታኝ በሶስተኛነት ተፈላጊ ሙያ በሚል ሲቀመጥ የኢንፎርሜሽን ደህንነት ተንታኝ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ምህንድስና ሙያዎች ደግሞ ሌሎቹ የቀጣይ ዘመን ተፈላጊ ሙያዎች እንደሆኑ ተገልጿል።
በመቀጠልም የዳታ ትንተና፣ ሮቦቲክ ምህንድስና ፣ ኤሌክትሪክ ምህንድስና ፣ የግብርና መሳሪያ ኦፕሬቲንግ እንዲሁም የድጅታል ትራንስፎርሜሽን ሙያ በተጨማሪነት የተለዩ የቀጣይ ዘመን ሙያ መስኮች ናቸው ተብሏል።
ይህ በዚህ እንዳለም በቴክኖሎጂዎች አዳዲስ ፈጠራዎች አማካኝነት ከገበያው ሊወጡ የሚችሉ ሙያዎች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው።
የባንክ ባለሙያዎች፣ ፖስተኛ፣ ካሸር፣ ቲኬት ቆራጭ እና የጽህፈት ሙያዎች በቴክኖሎጂዎች መስፋፋት ምክንያት ከገበያ የሚወጡ ሙያዎች እንደሚሆኑ ዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ ፎረም ገልጿል።
ድርጅቱ ከዚህ በተጨማሪም የሂሳብ ሙያ እና የቤት ለቤት ሽያጭ ሙያ በዚሁ በቴክኖሎጂዎች ከሚተኩ ሙያዎች ዝርዝር ውስጥ አስቀምጧቸዋል።