የፌስቡክ፣ ዋትስአፕ እና ኢንስታግራም እናት ኩባንያ ሜታ ከ10 ሺህ በላይ ሰራተኞቹን ቀንሷል
ሜታ ባለፈው ወር ከስራ እቀንሳቸዋለሁ ያላቸውን ሰራተኞች በይፋ በደብዳቤ ማሳወቅ ጀምሯል።
የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርክ ዙከርበርግ ፥ የሰራተኞች ቅነሳው ለሜታ ውጤታማነትና ዘላቂነት ወሳኝ ነው ብለዋል።
የፌስቡክ፣ ዋትስአፕ እና ኢንስታግራም እናት ኩባንያ ሜታ ባለፈው አመት 11 ሺህ የሚጠጉ ሰራተኞቹን ማሰናበቱ ይታወሳል።
ኩባንያው ባለፈው ወርም ተጨማሪ 10 ሺህ ሰራተኞችን እንደሚቀንስ ማሳወቁ አይዘነጋም።
ከትናንት ጀምሮ በይፋ ከኩባንያው የተሰናበቱት ሰራተኞች ደብዳቤ እየደረሳቸው ነው ያሉት ዙከርበርግ፥ እስከ ፈረንጆቹ አመት መጨረሻ ቆይተው የሚሰናበቱ እንዳሉበትም ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ስንብት ውስጥ የተካተቱት አብዛኞቹ ሰራተኞች በአይቲ እና ሰራተኛ ምልመላ ላይ የተሰማሩ ነበሩ ተብሏል።
በቀጣዩ ወርም በቢዝነስና አስተዳደር ዘርፍ የሚገኙ ሰራተኞች ቅነሳ እንደሚጀመር ሜታ አስታውቋል።
ከአሜሪካ ውጭ ባሉ ሀገራት ግን የተሰናበቱ ሰራተኞችን የማሳወቁ ሂደት ሊዘገይ እንደሚችል ነው ማርክ ዙከርበርግ ይፋ ያደረጉት።
ሜታ፣ ጎግል፣ አማዞንና ማይክሮሶፍትን ጨምሮ በርካታ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ባለፉት ወራት ከ170 ሺህ በላይ ሰራተኞችን ቀንሰዋል።
ሰራተኞችን መቀነሳቸው ከገጠማቸው መንገራገጭ እንደሚታደጋቸውም ኩባንያዎቹ ሲገልጹ ይደመጣል።
ሜታ ከስራ እንደቀነሳቸው ያወቁ ሰራተኞችም በፌስቡክና ኢንስታግራም ስራ ፍለጋ መጀመራቸው እየተነገረ ነው።