በነቀምቴ ከተማ የተፈጠረው ምንድን ነው?
ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራው ”ሸኔ” የታጠቀ ኃይል ትናንት ማለዳ በነቀምቴ ከተማ ላይ ጥቃት ከፍቷል
“ሸኔ” በተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ነዋሪዎች ተናግረዋል
የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የፈረጀው “ሸኔ” የምስራቅ ወለጋ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው የነቀምቴ ከተማ ላይ ጥቃት መክፈቱ ተነግሯል።
ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች ለአል ዐይን አማርኛ አንደገለጹት፤ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራው ”ሸኔ” ታጣቂዎች ትናንት እሁድ ጥቅምት 27 ቀን 2015 ዓ.ም ማለዳ ጀምሮ ተኩስ ከፍተው እንደነበር አስታውቋል።
በድንገት ማለዳ ላይ ከተማዋን በእሩምታ ያናወጠው የተኩስ ልውውጥ በሸኔ ታጣቂዎች እና በከተማ ውስጥ በሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት እንዲሁም የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች መካከል ንጋት ላይ መጀመሩንና ያለማቋረጥ እስከ ከሰዓት መዝለቁን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
ነቀምቴ ከተማ ትናንት ጠዋት ወደ ከተማው ዘልቀው ገብተው የነበረው ”ሸኔ” የታጠቀ ኃይል እስር ቤቶችን ሰብረው እስረኞችንም መልቀቃቸውን እንዲሁም የመንግስትና የግል ተቋማት ላይ ውድመት እና ዘረፋ መፈጸማቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የሸኔ ታጣቂ ቡድን ጥቃትን ተከትሎ በነቀሜቴ ከተማ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የኤሌክትሪክ አገለግሎት መቋረጡንም ነዋሪዎች አስታውቀዋል።
ሆኖም ከትናንት ከሰዓት ጀምሮ የተኩስ ድምጽ መቆሙን እና በከተማው መረጋጋት እንደሚታይ ነገር ግን በቤታቸው ውስጥ እንደሚገኙ ነው የአል ዐይን የመረጃ ምንጮች የገለጹት።
የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የክልሉ የፀጥታ ኃሎች በወሰዱት የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ከተማዋን ሙሉ በሙሉ የማረጋጋት እርምጃ እየወደ መሆኑንም ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት።
”ሸኔ” የታጠቀ ኃይል በነቀምቴ ከተማ ላይ በትናትናው እለት ከፍቶት የነበረውን ጥቃት አስመልክቶ ከፌደራል መንግስትም ይሁን ከኦሮሚያ ክልል መንግስት እስካሁን የተባለ ነገር የለም።