ድርጊቱን “ግዴለሽ” ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ተቀናቃኝ ወገኖችን አስጠንቅቀዋል
በሱዳን ቀውስ የአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ተሽከርካሪ ከፈጥኖ ደራሹ ጋር ግንኙነት አላቸዉ በተባሉ ተዋጊዎች ጥቃት ደርሶበታል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ድርጊቱን “ግዴለሽ” እና “ኃላፊነት የጎደለው” ብለውታል።
ቅዳሜ ዕለት በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል በተቀሰቀሰው ውጊያ በትንሹ 185 ሰዎች ሲሞቱ ከአንድ ሽህ 800 ሰዎች በላይ መቁሰላቸው ተነግሯል።
የስልጣን ሽኩቻው ሀገሪቱ ወደ ሲቪል አገዛዝ እንዳትሸጋገር እና የበለጠ ግጭት እንዳይፈጠርም ስጋት ፈጥሯል።
ብሊንከን በደረሰው ጥ የቃትአሜሪካን ባንዲራ እያውለበለበ የነበረ የዲፕሎማቲክ ኮንቮይ መቃጠሉን እና ውስጥ የነበሩ ሰዎች ደህና መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለጥቃቱ ቀጥታ ማስጠንቀቂያ የሰጡት ብሊንከን ሁለቱን የጦር አበጋዞች በተናጠል በአሜሪካ ዲፕሎማቶች ላይ የሚደርስ ማንኛውም አደጋ ተቀባይነት እንደሌለው ነግረዋቸዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
በጃፓን በተካሄደው የቡድን ሰባት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ስብሰባ ላይ ብሊንከን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "ስለ አጠቃላይ የጸጥታው ሁኔታ ጥልቅ ስጋት አለን" ብለዋል።
ብሊንከን ሁለቱም መሪዎች የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ አሳስበዋል።
"የሲቪሎችን፣ የዲፕሎማቲክ እና የሰብዓዊ ሰራተኞችን ደህንነት የማረጋገጥ ኃላፊነት አለባቸው" ሲሉም የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ገልጸዋል።