በሱዳን ጉዳይ የሃያላን ሀገራት ፍላጎትና አሰላልፍ ምን ይመስላል?
4ኛ ቀኑን በያዘው የሱዳን ግጭት የሩሲያ እና አሜሪካ ስም በተለያየ መንገድ እየተነሳ ነው
የሃያላኑ የፍላጎት ተቃርኖ ካርቱምን የእጅ አዙር ጦርነት መፋለሚያ ሜዳ ያደርጋት ይሆን ?
የሱዳን ጦርና የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ (አርኤስኤፍ) ውጊያ ዛሬ አራተኛ ቀኑን ይዟል።
አሜሪካና ሩሲያን ጨምሮ በርካታ ሀገራትም ተፋላሚዎቹ ተኩስ አቁመው ወደ ድርድር እንዲመጡ ጥሪ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል።
ለግጭቱ የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ወደ ብሄራዊ ጦሩ መቀላቀል አለመፈለጉ እንደምክንያት ቢነሳም ከጀርባ በርካታ ገፊ ምክንያቶች እንዳሉ ተንታኞች ያምናሉ።
ከ2019ኙ መፈንቅለ መንግስት ወዲህ የሲቪል አስተዳደር ለመትከል ሞክራ ወዲያው የከሸፈባት ሀገር አደባባዮቿ ሰርክ በተቃውሞ ሰልፎች ቢሞሉም መረጋጋት አልቻለችም።
ምርጫ እስኪደረግ ድረስ የሽግግር መንግስት ለመመስረት ፖለቲከኞቿ ሲያደርጉት የከረሙት ውይይትም ወደ ፍጻሜው ሲቃረብ ኦማር ሀሰን አልበሽርን በጋራ ያስወገዱት ጀነራሎች በጠላትነት ተፈራርጀው ጦር ተማዘዋል።
በሁለቱም ወገን ያሉ “አይዞህ ባዮች” የምስራቅ አፍሪካዊቷን ሀገር መከራ ስለማብዛታቸው ነው የሚነገረው።
የሱዳን ጦር አዛዡ አብዱልፈታህ አልቡርሃን እና የአርኤስኤፍ መሪው ጀነራል ሃምዳን ዳጋኦ (ሄሜቲ) ልዩነት እንዲሰፋም የተለያየ ፍላጎት ያላቸው ሀገራት ድርሻ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ተንታኞች ይሞግታሉ።
ሩሲያ
ሩሲያ ኦማር ሃሰን አልበሽር በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣናቸው ከመነሳታቸው በፊት ከሱዳን ጋር አንድ ስምምነት ፈጽማለች፤ በፖርት ሱዳን ወታደራዊ ማዘዣ መገንባት የሚያስችል ስምምነት።
ስምምነቱ ሞስኮ 300 ወታደሮች እና አራት የጦር መርከቦቿን የምታሰፍርበትና በቀይ ባህር ቅኝት የምታደርግበትን እድል የሚፈጥር ነው።
ለ25 አመት ይቆያል የተባለው ስምምነት ካርቱምን ከሩሲያ የጦር መሳሪያ እንድታገኝ የሚያደርግ እንደነበርም አሶሼትድ ፕረስ በዘገባው ያወሳል።
ይህ ስምምነት በፓርላማ ሳይጸድቅ ግን አልበሽር በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣናቸው ተነስተዋል።
ሞስኮ ባለፉት አመታት ከሱዳን ወታደራዊ መሪዎች ጋር በስምምነቱ ዙሪያ ስትመክር ቆይታለች።
የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ መሪ ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎም ለአንድ ሳምንት በሞስኮ ቆይታ አድርገው ሲመለሱ አዎንታዊ ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል።
ሄሜቲ በዚህ ጉብኝታቸው ከቭላድሚር ፑቲን ሀገር የተገባላቸው ቃል ባይገለጽም የኦማር ሃሰን አልበሽር አስተዳደር ቀደም ብሎ የጠየቀው የጦር መሳሪያ ድጋፍ በአጻፋው እንደሚሰጣቸው የሚገምቱ ተንታኞች አሉ።
የሩሲያው የወጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በሱዳን ባደረጓቸው ጉብኝቶችም የወታደራዊ ጣቢያው ጉዳይ ዋነኛ መነጋገሪያ ርዕስ እንደነበር የሮይተርስ ዘገባ ያመላክታል።
ባለፈው ቅዳሜ ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ የሚመሩት ፈጥኖ ደራሽ ሃይል ከሱዳን ጦር ጋር መፋለም ሲጀምር የሩሲያ ስም አብሮ እየተነሳ ነው።
የሩሲያው ቅጥረኛ ወታደሮች አቅራቢ ዋግነር ለሄሜቲ ከለላ እየሰጠ ነው የሚሉ ሪፖርቶችም ወጥተዋል።
በሱዳን የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ግን ሁለቱም ወገኖች ግጭት አቁመው ወደ ጠረጼዛ ዙሪያ ንግግር እንዲመለሱ ከመጠየቅ ውጪ ለሚቀርቡ ወቀሳዎች ምላሽ አልሰጠም።
አሜሪካ
አሜሪካ የሱዳን ወቅታዊ ሁኔታን በቅርበት እየተከታተልኩ ነው ብላለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አንቶኒዮ ብሊንከንም ከጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን እና ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ ጋር በስልክ መምከራቸው ተገልጿል።
በውይይቱ በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለማንቀሳቀስና ንጹሃንን ለመጠበቅ ለ24 ስአት ተኩስ ለማቆም ተስማምተናል ያሉት ሄሜቲ፥ የአልቡርሃን ጦር ድብደባውን ገፍቶበታል ሲሉ ከሰዋል።
ይህንን አለማቀፍ ህግ የመጣስና ሌሎች ጉዳዮች በተመለከተ ከአሜሪካ ጋር በቀጣይ እንመክርበታለን የሚል መልዕክታቸውንም በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ይህም ከዋሽንግተን የተለየ ድጋፍ ያላቸው መስሎ መታየትን መፈለጋቸውን አልያም ከብሊንከን ጋር ባደረጉት ውይይት የተገባላቸው ቃል ስለመኖሩ የሚያመላክተው ነገር እንደሚኖር ይታመናል።
የዋሽንግተን ግልጽ አሰላለፍ እስካሁን በይፋ ባይገለጽም ፍላጎቷ ግን ግልጽ ነው፤ ሩሲያ በፖርት ሱዳን ልትገነባው ያሰበችውን ወታደራዊ ጣቢያ ከንቱ ማድረግ። ለዚህም አሸናፊ ይሆናል ብላ ላመነችበት ሃይል ድጋፍ ልታደርግ እንደምትችል ነው ወታደራዊ ተንታኞች የሚያነሱት።
ሄሜቲ ከሁለቱ ባላንጣ ሃያላን ሀገራት ድጋፍ እንዳላቸው ቢነገርም ወይም መስለው ቢታዩም፥ የሱዳንን ጦር የሚመሩት ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃንም በፊናቸው አጋር አላቸው።
ከአሜሪካ እና ሩሲያ ባሻገር የጎረቤት እና የቀጠናው ሀገራት ፍላጎትና የሃይል አሰላለፍ ሱዳንን እንደ ዩክሬን የሃያላኑ የእጅ አዙር መፋለሚያ ምድር እንዳያደርጋት ያሰጋል።
የሱዳናውያን የለውጥ አቢዮት በውጭ ሃይላት ጣልቃገብነት እንዳይጠለፍም ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል እየተባለ ነው።