የጉበት በሽታ (ሄፕታይተስ) ምንድነው፤ መከላከያው እና ህክምናውስ?
ጉበት በሰውነታችን ውስጥ የሰውነት ክፍሎቻችን ከሚገኙት ትልቁ ሲሆን፤ ቅርጹ ወደ ሦስት ማእዘን ያደላል። በውስጡ 300 ቢሊዮን የሚደርሱ ሴሎች ያሉት ሲሆን እነርሱም በደም ቧንቧ ውስጥ ሁነኛ ስራ ያላቸው ናቸው።
የጉበት በሽታ ምንድነው፤ መከላከያው እና ህክምናውስ? በሚለው ዙሪያ ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካ ኮሌጅ ያገኘነውን መረጃ እንደሚከተለው ቀርቧል።
የጉበት በሽታ እንዴት ይከሰታል?
የጉበት በሽታ (ሂፕታይትስ) የሚከሰተው በጉበታችን ውስጥ ያሉ ሴሎች በሽታ አምጪ በሆነው ቫይረስ ሲጠቁ ነው።
እንዲሁም የአልኮል መጠጥና ሌሎች መርዛማነት ካላቸው ነገሮች እና አንዳንድ መድኃኒቶች የሚያመጧቸው የጎንዮሽ ችግሮች በሽታ ሊከሰት ይችላል።
በቫይረስ የሚከሰተው የጉበት በሽታ ዓይነቶች ዋንኞቹ አምስት ሲሆኑ፤ እነዚህም የጉበት በሽታ ኤ፣ የጉበት በሽታ ቢ ፣ የጉበት በሽታ ሲ፣ የጉበት በሽታ ዲ እና የጉበት በሽታ ኢ ተብሎ ይጠራል።
የጉበት በሽታ ኤ (ሂፕታይተስ ኤ)
ሂፕታይተስ ኤ በአብዛኛው የሚከሰተው በንጽህና ያልተዘጋጀ ምግብ በመመገብ ወይም ንጹህ ውሃ ባለመጠጣት ነው። ይህ አይነቱ የጉበት በሽታ ንፁህ ውሃና ፅዱ አካባቢ በማይኖሩ ሰዎች ዘንድ ማየቱ የተለመደ ነው።
መከላከያው፡- የግል የአካባቢ ንፅህና በመጠበቅ እንዲሁም ንፁህ ውሃ በመጠጣት በሽታውን መከላከል ይቻላል። ባደጉት ሃገራት ግን ክትባቱ ይገኛል።
የጉበት በሽታ ቢ (ሂፕታይተስ ቢ)
ሂፕታይተስ ቢ ሊያገኘን የሚችለው በበሽታው ከተያዘ ሰው ደም ወይም ከሰውነቱ ከሚወጣው ፈሳሽ ጋር ንክኪ ሲኖር ነው።
ለምሳሌ በጥንቃቄ ያልተያጸጉር ወይም ጺም በጋራ ምላጭ ወይም መሳሪያ የሚጠቀሙ፣የጋራ የጥርስ ብሩሽ፣ የልቅ የግብረ ስጋ ግንኙነት የሚያደርጉ ሰዎች የጉበት በሽታ ቢ በቀላሉ ያገኛቸዋል።
ሂፕታይተስ ቢን በክትባት መከላከል የሚቻል ሲሆን፤ የጺም ወይም ፀጉር መላጫዎችን፣ የጥርስ ብሩሽ፣ የጥፍር መቁረጫዎችን በጋ ባለመጠቀም በሽታውን መከላከል ይቻላል።
ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑሰዎች ክትባቱን ቢወስዱ ይመከራል።
የጉበት በሽታ ሲ (ሂፕታይተስ ሲ)
ሄፒታይተስ ሲ ማለት መንስኤው ሄፒታይተስ ሲ ቫይረስ የሆነ የጉበት ህመም ማለት ሲሆን፤ አንድ ሰው በህመሙ ከተያዘ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ወራት የሚከሰት ነው።
የሂፕታይተስ ሲ ዋናው መከላከያ መንገድ ለበሽታው የሚያጋልጡ ነገሮችን ማስወገድ ነው።
በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር በጋራ የምንጠቀምባቸውን ማንኛውም ነገር ማቆም መፍትሄ የሚሆን ሲሆን፤ ህክምና ወደሚሰጥበት ጤና ተቋም በመሄድ ሄፒታይተስ ሲ ቫይረስ ሊያድኑ የሚችሉ አዳዲስና ፍቱን መድሃኒት ማግኘት ይችላሉ።
የጉበት በሽታ ዲ (ሂፕታይተስ ዲ)
የጉበት በሽታ ዲ የሚባለው በቀጥታ የጉበት በሽታ ቫይረስ በተበከለ ደም አማካኝነት ይተላለፋል፡፡ ይህ በሽታ የሚታየው በጉበት በሽታ ቢ ለተያዘ ብቻ ነው።
መከላከያው፡- የግል መጠቀሚያ የሆኑትን የጥርስ ብሩሽ፣ የፂም መላጫ መሳሪያዎችን፣ የጥፍር መቁረጫ ቁሳቁሶችን በጋራ አለመጠቀም እንደ ሁነኛ ቅድመ መከላከያ ተደርጎ ይወሰዳል።
የጉበት በሽታ ኢ (ሂፕታይተስ ኢ)
ይህ በሽታ ዋናው መተላለፊያው መንገድ በጉበት በሽታ የታመመ ሰው ዓይነ ምድር የተበከለ ውሃ በመጠጣት ወይም ምግብ በመመገብ ነው።
መከላከያው፡- መፍትሔው የራስንና የአካባቢን ንጽህና መጠበቅ ነው። በተለይ ንጽህናው ካልተጠበቀ ቦታ የሚመጣን ውሃ ፈጽሞ አለመጣት ራስን ከጉበት በሽታ ማዳን እንደሆነ ማወቅ ይገባል።