በአሜሪካ አንድ ግለሰብ የአሳማ ልብ ተገጠመለት
የአሜሪካ ዶክተሮች የልብ ታማሚውን ግለሰብ ህይወት ለመታደግ ሲሉ ልቅለ ተከላውን ማሄዳቸውን አስታውቀዋል
የአሳማ ልብ የተገጠመለት ግለሰብ በመልካም ጤንነት ላይ መሆኑ ታውቋል
በአሜሪካ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የአሳማ ልብን ለሰው የመግጠም የተሳካ የንቅለ ተከላ ቀዶ ህክምና መካሄዱ ተሰምቷል።
በአሜሪካዋ ሜሪላንድ ከተማ በሚገኝ ሆስፒታል በተካሄደው ህይወት አድን ቀዶ ጥገናው ስኬታማ ነበር ያሉት ዶክተሮቹ፤ ታካሚው የአሳማ ልብ ከተገጠመለት ሶስት ቀን እንደሞላው እና በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል።
ቀዶ ጥገናው ሙሉ በሙሉ የተሳካ ነው ብሎ ለመናገር ገና ነው ያለው የሜሪላንድ የህክምና ማእከል፤ የእንስሳት አካላትን ለሰዎች ለመጠቀም ለአስርት ዓመታ ሲካሄድ የነበረውን ጥናት ግን አንድ እርምጃ ወደ ፊት ማራመድ የቻለ ነው ተብሏል።
የሜሪላድ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ማእከል ዶክተሮች የበራሄ (ጄኔቲካል) ማስተካከያ የተደረገለት የአሳማ ልበን ለታካሚው የሰጡ ሲሆን፤ የግለሰቡ ሰውነትም የአሳማውን ልብ መቀበሉ ነው የተነገረው።
የአሳማ ልብ የተገጠመለት ታካሚ የ57 ዓመቱ ዴቪድ ብኔት የሚባል ሲሆን፤ የአሳማ ልብ ንቅለ ተከላው ሊሳካም ላይሳካም እንደሚችለል ያውቃል ተብሏል።
ለታካሚው የሚሆን ወይም የሚስማማ የሰው ልብ በመታጣቱ የአሳማ ልብ እንደተገጠመለት የተነገረ ሲሆን፤ ወደ ሞት እየተቃረበ ስለሆነ እና ምንም አማራጭ ስላልነበረ የአሳማውን ልብ መሞከሩን የታካሚው ልጅ ለኤ.ፒ ተናግሯል።
ታካሚው ዴቪድ ብኔት የልብ ቀዶ ህክምናውን ከማድረጉ በፊት በሰጠው አስተያየት፤ “የነበረኝ አማራጭ ይህንን የልብ ቀዶ ጥገና ማድረግ አሊያም መሞት ነው፤ ይህ የመጨረሻ አማራጬ መሆኑንም አውቃለሁ” ብሏል።
ከትናንት ሰኞ ጀምሮ ታካሚው ብኔት በራሱ መተንፈስ የጀመረ ሲሆን፤ አዲሱ ልቡን ለማገዝ ግን አጋዥ መተንፈሻዎች ተገጥመውለታል።
ብኔት እያገገመ በሚሄድበት በቀጣይ ሳምንታትም ዶክተሮች በቅርብ ክትትል እንደሚያድርጉለት አስታውቀዋል።
የቀዶ ጥገና ህክምውን የመሩት ዶ/ር መሃመድ ሙህዲን፤ አሁን ላይ በአሜሪካ ልብን ጨምሮ ለሰዎች የሚለገሱ የሰውነት አካላት እጥረት መኖሩን አንስተው፤ ይህ ህክምና ከተሳካ ግን በህመመም ለሚሰቃዩ ሰዎች በቂ አቅርቦት ይኖራል ብለዋል።
የኒውዮክ ዶክተሮች ባለፍነው የፈረንጆቹ 2021 ቀደም ባደረጉት የተሳካ ንቅለ ተከላ የአሳማ ኩላት ለሰው መግጠማቸው ይታወሳል።