ግለሰቡ መከተብ ለማይፈልጉ ሰዎች ሀሰተኛ የክትባት ማስረጃ ለመሸጥ ነው የተከተበው
ከተቀመጠው ገደብ በላይ በተደጋጋሚ በርካታ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባቶችን የተከተቡት ጀርመናዊው አዛውንት በፖሊስ መያዛቸው ተሰምቷል።
የ60 ዓመቱ ጀርመናዊ አዛውንት መከተብ ለማይፈልጉ ሰዎች ሀሰተኛ የምስክር ወረቀት ለመሸጥ ሲል በተደጋጋሚ መከተባቸው ተሰምቷል።
በምስራቅ ጀርመን በምትገኘው ማግድበርግ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አዛውንቱ በጀርመኗ ሳክሶኒ ግዛት በመሄድ ለወራት የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባ ሲከተቡ መቆየታቸው ተነግሯል።
ግለሰቡ በፖሊስ እስከሚያዙ ድረስ ከ90 በላይ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባቶችን መከተባቸውም የጀርመን ዜና ኤጀንሲ (ዲ.ፒ.ኤ) ዘግቧል።
ግለሰቡ ክትባቶቹን በተደጋጋሚ የተከተቡት፤ መከተብ ለማይፈልጉ ሰዎች የተጭበረበረ የምስክር ወረቀት ለመሸጥ እንደሆነም ነው የተነገረው።
በዚህም በሚከተቡበት ጊዜ የሚወስዱትን ትክክለኛ የክትባት ቁጥር በያዙት ተመሳሳይ ካርድ ላይ በመሙላት እና ስም በመቀየር ሲሸጡ ነበር ተብሏል።
ግለሰቡ በሳክሶኒ ግዛት ውስጥ በተከታታይ ለሁለተኛ ቀን ሊከተቡ ሲሉ በፖሊስ የተያዙ ሲሆን፤ በእጃቸው ላይም የተለያዩ ሀሰተኛ ካርዶች እና ትክክለኛ የክትባት ቁጥሮች መገኘታቸው ተነግሯል።
ተጠርጣሪው ወደ እርስ ቤት ያልተወሰዱ ሲሆን፤ ባሉበት ሆነው በጉዳዩ ላይ ፖሊስ ምርመራ እያደረገ መሆኑ ታውቋል።
የ60 ዓመቱ አዛውንት የተከተቡት 90 ክትባቶች የተለያዩ አይነቶች ናቸው የተባለ ሲሆን፤ በጤናቸው ላይ ምን አይነት ጉዳት ሊያስከትል ይችላል የሚለውም በጤና ባለሙያዎች እየታየ መሆኑ ተነግሯል።