ለጤናችን እጅግ ጠቃሚ የሆነው አድኖሲን ምንድን ነው?
ካፌይን አብዝተው በሚጠቀሙ ሰዎች ላይ ጉዳት ይኖረው ይሆን?
የሰው ልጅ በቀን ምን ያህል ቡና ነው መጠጣት ያለበት?
አድኖሲን የሚባለው ኬሚካል በሰውነታችን አካል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በተለይም ዋና ስራው በቂ እርፍት እንድናደርግ የድካም ስሜት ወደ አዕምሯችን መላክ ነው፡፡
በዚህ ጊዜ አዕምሮ የተለያዩ የድካም መልዕክቶችን ወደ ሰውነታችን የሚያስተላልፍ ሲሆን ማዛጋት፣ እንቅልፍ እንቅልፍ ማለት፣ የሰውነት መዛል እና ሌሎችም ምልክቶች የዚህ አድኖሲን የተሰኘው እና በሰውነታችን ውስጥ የሚመነጨው ኬሚካል ውጤቶች ናቸው፡፡
በዚህ ጊዜ ሰዎች የድካም ስሜታቸውን ለማስታገስ እንዳሉበት ሁኔታ እርምጃ የሚወስዱ ሲሆን እረፍት ማድረግ፣ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ፣ ምግብ እና ውሀ መውሰድን ጨምሮ ሌሎችንም እርምጃዎች ይወስዳሉ፡፡
ለነዚህ ሁሉ እርምጃዎች አድኖሲን የተሰኘው ኬሚካል ለአዕምሯችን ያስተላለፈው የድካም ስሜት መልዕክት ውጤቶች ሲሆን ሰዎች የድካም ስሜቶችን ለማስወገድ ቡናን በመውሰድ ይታወቃሉ፡፡
ካፌይን የተሰኘ አነቃቂ ንጥረ ነገር የያዘው ቡና ወደ ሰውነታችን ሲገባ አድኖሲን ወደ አዕምሯችን የድካም ስሜቶችን እንዳያስተላልፍ እና ሰውነታችን የድካም ስሜት እንደሌለበት እንዲሰማው በማድረግ ይታወቃል፡፡
በዚህ ጊዜ ነው የሰው ልጅ በቀን ምን ያህል ቡና ቢጠጣ ነው የጎንዮሽ ጉዳቶች የማያስከትለው? የሚለው ጉዳይ በየጊዜው ጥናት እየተደረገበት ይገኛል፡፡
ቡናን መጠጣት በርካታ የጤና በረከቶች ያሉት ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ወደ አዕምሯችን በቂ ደም እንዲዘዋወር፣ የልብ ምታችን እንዲስተካከል፣ ጭንቀት ፣ ድባቴ፣ የመርሳት በሽታን መቀነስ እና ሌሎችንም ጥቅሞች እንደሚያስገኝ ቢቢሲ የአውሮፓ ምግብ ደህንነት ባለስልጣን ያስጠናውን ጥናት ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡
በአንድ ሲኒ 928 ሚሊ ግራም ካፌይን ያለው የዓለማችን በጣም ጠንካራው ቡና…
እንደ ዘገባው ከሆነ በአማካኝ አንድ ሰው በቀን ከ400 ግራም በላይ ካፌይን ወይም ከሶስት ስኒ በላይ ቡና ከጠጣ ረፍት አልባ ስሜቶችን ማስተናገድ ጨምሮ ሌሎች ጉዳቶችን ሊያስከትል ይችላል፡፡
ነፍሰ ጡሮች ደግሞ በቀን ከ200 ግራም በላይ ካፌይን እንዳይወስዱ የሚመከሩ ሲሆን ከተጠቀሰው መጠን በላይ ከወሰዱ ግን ጨጓራን ጨምሮ ለሌሎች የሆድ እቃ ህመሞች ሊዳርጋቸው ይችላል ተብሏል፡፡
ከፍተኛ ካፌይን መጠቀም ግን ወደ አዕምሯችን የሚሄደውን የደም መጠን በመጨመር ለከባድ ራስ ምታት ወይም ማይግሪን፣ ኩላሊት ህመም እና ሌሎች የጎንዮሽ ጉዳቶችን ሊያደርስ እንደሚችል ተገልጿል፡፡
በተለይም የቡናውን ጣዕም ለማሻሻል በሚል እንደ ስኳር እና ሌሎች ግብዓቶችን ደጋግሞ መጠቀም ለሌሎች ተያያዥ የጤና እክሎች ሊዳርግ ይችላልም ተብሏል፡፡