ዋትስአፕ የተጠቃሚዎችን መረጃ ለሦስተኛ ወገን ላለመስጠትም ቃል ገብቷል
የቴክኖሎጂ ኩባንያው ዋትስአፕ የአውሮፓ ህብረት ህግን በማክበር የአገልግሎት ውሉን ለመቀየር መስማማቱ ተነግሯል።
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን እንዳስታወቀው፤ ከህብረቱ የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣናት እና ከአውሮፓ ኮሚሽን ጋር የተደረገ ውይይትን ተከትሎ መተግበሪያው በአገልግሎት ውሉ ላይ የሚደረጉ ለውጦችን የበለጠ ግልጽ ለማድረግ ተስማምቷል።
ዋትስአፕ ከአሁን በኋላ በተጠቃሚዎች ውል ውስጥ ምን ለመለወጥ እንዳሰበ እና ከተጠቃሚዎች መብት ጋር እንዴት እንደሚገናኝ በግልጽ ያብራራል ተብሏል።
እንዲሁም መተግበሪያውን ማዘመንን በተመለከተ ለተጠቃሚዎች አማራጭ እንደሚሰጥ አናዶሉ ዘግቧል።
በተጨማሪም ንብረትነቱ የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያ የሜታ የሆነው ዋትስአፕ፤ የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮችን ጨምሮ የተጠቃሚዎችን መረጃ ለሦስተኛ ወገኖች ላለማካፈል ቃል ገብቷል።
የአውሮፓ ህብረት የፍትህ ኮሚሽነር ዲዲየር ሬይንደርስ "ተጠቃሚዎች የተስማሙበትን ጉዳይ እና ምርጫው በተጨባጭ ምን እንደሚያካትት የመረዳት መብት አላቸው" ብለዋል።
የአውሮፓ ባለስልጣናት ከሸማቾች ጥበቃ ማህበራት በደረሰ ማስጠንቀቂያ በፈረንጆቹ ጥር 2022 በዋትስአፕ ላይ ምርመራ ከፍተዋል።
ዋትስአፕ ስምምነት ያደረገው ምርመራውን ተከትሎ ነው።