የሜታ እህት ኩባንያ የሆነው ዋትስአፕ ተጠቃሚዎቹ ይበልጥ የሚቀራረቡበትን እና ያሉበትን ሁኔታ የሚያጋሩበት እድል ፈጥሯል
ዋትስአፕ ምስልና ድምፅ ማጋራት ጀመረ።
ግዙፉ የመልዕክት መለዋወጫ የትስስር ገፅ ዋትስአፕ ደንበኞቹን ይበልጥ ለማቀራረብ እየሰራ ይገኛል።
በትናንትናው እለትም የትስስር ገፁ ተጠቃሚዎች ያሉበትን ሁኔታ እና ስሜታቸውን የሚያጋሩበትን አማራጭ አስተዋወቋል።
ዋትስአፕ ደንበኞቹ ለ24 ሰአት የሚቆዩ ምሰሎችን የሚያጋሩበትን እድል ነው የፈጠረው።
በዚህም በስልካቸው የተመዘገቡትም ሆነ ሌሎች የዋትስአፕ ተጠቃሚዎች አስተያየት ሊያጋሯቸው ይችላሉ።
ከ30 ሰከንድ ያልበለጠ የድምፅ ቅጂንም ማጋራትና ሀሳብ መለዋወጥ እንደሚቻል ነው ኩባንያው ያስታወቀው።
ያሉበትን ስሜት ወይም ሁኔታ በምስልና በድምፅ የሚያጋሩ የዋትስአፕ ተጠቃሚዎች የለጠፉትን ማን መመልከት እንደሚችል መወሰንም ያስችላል አዲሱ የመተግበሪያው ማሻሻያ።
የዋትስአፕ ተጠቃሚዎች ከምስልና ድምፅ ባሻገርም ፅሁፍና ቪዲዬዎችን በአንድ ጊዜ ለመላው የዋትስአፕ ተጠቃሚ በማጋራት ይበልጥ መግባባትና ሃሳብ መጋራት ይችላሉ ነው ያለው ኩባንያው።
ዋትስአፕ የተጠቃሚዎቹን ፍላጎት ይበልጥ ለማርካትም ስሜትን የሚገልፁ (ኢሞጂዎችን) በስፊ አማራጭ ይዞ መምጣቱን አስታውቋል።
ለሚጋሩት ጉዳዬች በፅሁፍ፣ በኢሞጂ እና ድምፅ ምላሽ መስጠት እንደሚቻልም ነው የገለፀው።
ከምንም በላይ ግን የሚጋሩት ምስሎችም ሆነ መልዕክቶች ከሶስተኛ ወገን ጣልቃገብነት ነፃ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንፈልጋለን ብሏል ዋትስአፕ በመግለጫው።
ከ2 ቢሊየን በላይ ወርሃዊ ተጠቃሚ ያለው ዋትስአፕ ደህንነቱ የተጠበቀ የመረጃ ልውውጥ ስርአት መዘርጋቱ ይነገርለታል።
ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካና ናይጀሪያ በርካታ የዋትስአፕ ተጠቃሚ ያለባቸው ሀገራት ናቸው።