ቴሌግራም ዋትስአፕን በመብለጥ በሩሲያ ቀዳሚ መልእክት መላላኪያ ሆነ
የሩሲያ ባለስልጣናት ቴልግራም እያበረታቱ ሲሆን እንደ ኢንስታግራምና ፌስቡክ ያሉ አገልግሎቶችን እያገዱ ነው
በሩሲያ የዋትስአፕ ድርሻ ከ48 በመቶ ወደ 32 በመቶ ዝቅ ብሏል
ሩሲያ የተወሰኑ የዲጂታል አገልግሎቶችን ማገዷን ተከትሎ ቴሌግራም ዋትስአፕን በመብለጥ በሩሲያ ቀዳሚ መልእክት መላላኪያ መሆኑን ሜጋፎን የተባለው የሞባይል ኦፕሬተር ማስታወቁን ሮይተርስ ዘግቧል።
የዋትስአፕ ባለቤት የሆነው እና ፌስቡክን የሚያስተዳድረው የሜታ ፕላትፎርም ኢንክ (ኤፍ.ቢ.ኦ) በሩሲያ ፍርድ ቤት ክስ ውስጥ ገብቷል፣ አቃብያነ ህጎች ድርጅቱን “አክራሪ ድርጅት” በማለት ሊፈርጁት ይፈልጋሉ ተብሏል።
የሩሲያ ባለስልጣናት ሩሲያውያን ቴልግራምን እንዱጠቀሙ እያበረታቱ ሲሆን፤ እንደ ኢንስታግራም እና ትዊተር ያሉ አገልግሎቶችን በማገድ ላይ ናቸው።
ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችው ወታደራዊ ዘመቻ በውጭ ሀገራት ዲጂታል መድረኮች እና በሩሲያ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ላይ ነዳጅ ጨምሯል።
ከሩሲያ አራቱ ዋና የቴሌኮም ኦፕሬተሮች አንዱ የሆነው ሜጋፎን በተንቀሳቃሽ ስልክ የኢንተርኔት ትራፊክ ላይ ባደረገው ትንተና የቴሌግራም ድርሻ በመጋቢት ሁለት ሳምንታት ውስጥ በየካቲት ወር የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ከነበረበት 48 በመቶ ወደ 63 በመቶ ጨምሯል ብሏል።
ሜጋፎን እንደገለጸው የዋትስአፕ ድርሻ ከ48 በመቶ ወደ 32 በመቶ ዝቅ ብሏል። አማካኝ የቴሌግራም ተጠቃሚ በቀን 101 ሜጋ ባይት ዳታ የሚወስድ ሲሆን ለዋትስአፕ 26 ሜጋ ባይት ነው።
በሩሲያ ፓቬል ዱሮቭ የተመሰረተው ቴሌግራም በሩሲያ ውስጥ ከሞላ ጎደል ሁሉም ዋና ዋና ሚዲያዎች፣ የመንግስት አካላት እና የህዝብ ተወካዮች የይዘት ማሰራጫ አድርገው እየተጠቀሙበት ነው።
ሌሎች መልእክት መላላኪያ አገልግሎቶች በሩሲያ መታገዳቸውን ተከትሎ ቴሌግራም ተወዳጅ እየሆነ መምጣቱን ሜጋፎን በመግለጫው አስታውቋል።
አገልግሎቱ በፍጥነት ማደግ የጀመረው ሩሲያ በጎረቤቷ ዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረችበት ከፈረንጆቹ የካቲት 24 2022 ወዲህ ነው።
ሜታ ኩባንያ በዩክሬን ውስጥ የሚገኙ የኢንስታግራም ተጠቃሚዎች “ሞት ለሩሲያ ወራሪዎች” የሚሉ እና መሰል መልእክቶችን እንዲያሰራጩ መፍቀዱን ተከትሎ ሩሲያ ኢንስታግራም በሀገሯ እንዳይሰራ ማገዷ ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎም የሩሱያ የቴክኖሎጂ ዘርፍ የስራ ፈጣለሪዎች ከኢንስታግራም ጋር ተመሳሳይነት ያለው “ሮስግራም” የተባለአዲስ የማህበራዊ ትስስር ገጽ መተግበሪያ መስራታቸው ይታወሳል።