ዋትስአፕ ኢንተርኔት ቢቋረጥም ተጠቃሚዎች መልእክት እንዲላላኩ የሚያስችል አገልግሎት ሊጀምር ነው
መንግስታት ኢንትኔትን በሚዘጉበት ሰዎች አስቸኳይ እርዳታ እንዳያገኙ መብታቸውን እየጋፉ እንደሆነም ኩብንያው አስታውቋል
ሜታ ኩባንያ “መንግስታት ኢንተርኔት ቢዘጉም የተጠቃሚዎቼ ግንኙነት ግን አይቋረጥም” ብሏል
የጽሁፍ፣ ድምጽ፣ የፎቶ ግራፍ እና ተንቀሳቃሽ ምስል መላላኪያ የሆነው የማህበራው ትስስር ገጹ ዋትስአፕ ኢነተርኔት ቢዘጋም ሰዎች መልእክት እንዲላላኩ ላደርግ ነው አለ።
ዋትስአፕን የሚያስተዳድረው ሜታ ኩባንያ እንዳስታወቀው፤ “ከዚህ በኋላ መንግስታት ኢንተርኔት ቢዘጉም የተጠቃሚዎቼ ግንኙነት ግን አይቋረጥም” ብሏል።
የመልእክት መላላኪያ የሆነው ዋትስአፕ ኢንተርኔት በሚዘጋበት ወቅት በፕሮክሲ ሰርቨር (ከሀገሪቱ ቁጥጥር ውጪ በሆነ እና በውጭ በሚገኝ ሰርቨር) አማካኝነት ተጠቃሚዎች መካከል የመልእክት ልውውጥ እንዲኖር የሚያስቸል አዲስ አገልግሎት ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል።
በሜታ ኩባያ ስር የሚተዳደረው ግዙፉ የመልክት መላላኪያ መተግበሪያ ዋትስአፕ ከዚህ በኋላ በቅርቡ በኢራን እንዲሁም በተለያዩ የዓለም ሀገራት ውስጥ የሚታዩ የኢንተርኔት መዘጋቶች በዋትስአፕ መልእክት መላላክን አያግዱም ብሏል።
ኢንተርኔትን የሚዘጉ አካላት ሰብአዊ መብቶችን በመንፈግ ሰዎችን አስቸኳይ እርዳታ እንዳያገኙ እያደረጉ ነው ሲልም ዋትስአፕ ይከሳል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፕሮክሲ ሰርቨሮችን በፍቃደኝነት ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ያቀረበው ዋትስአፕ፤ ፕሮክሲ ሰርቨሮችን እንዴት ማዋቀር እንደሚቻል መመሪያ እሰጣለሁም ብሏል።
በፕሮክሲ ሰርቨር በኩል የሚደረጉ ግንኙነቶች እና የመልእክት ልውውጦች ሚስጥራዊነት እና የመረጃ ደሀንነት በከፍተኛ ደረጃ የሚጠበቁ መሆኑነም ዋትስአፕ በብሎግ ፖስቱ አስታውቋል።
ዋትስአፕ መተግበሪያ በዓለማችን ሁለት ቢሊዮን ተጠቃሚዎች ያሉት ሲሆን አውሮፓ፣ አሜሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና አፍሪካ ብዙ ተጠቃሚዎች እንዳሉት ይገለጻል።