በሙከራ ላይ ናቸው የሚባሉት የኮሮና ክትባቶች እውን ተስፋ ሰጪ ናቸውን?
በሙከራ ላይ ናቸው የሚባሉት የኮሮና ክትባቶች እውን ተስፋ ሰጪ ናቸው? መቼስ ይደርሳሉ?
መላው ዓለምን በማስጨነቅ ላይ ላለው የኮሮና ወረርሽኝ መላ ለመዘየድ ሃገራት ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችሉ የተለያዩ የመድኃኒት ዓይነቶችን ለማዘጋጀትም በከፍተኛ ጥረት ብቻም ሳይሆን በመሽቀዳደም ውስጥ ናቸው፡፡ ለዚህም ቻይናን፣አሜሪካን፣ጀርመንን እና እንግሊዝን እንዲሁም እስራኤልን መሰል ሃገራትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ትናንት የወጡ ዘገባዎች ጀርመን ለኮሮና ክትባቶች ፍቃድ ሰጠች የሚል መረጃን አንግበዋል፡፡
ክትባቶቹ ወደ ክሊኒካዊ የሙከራ ደረጃዎች እንዲሸጋገሩ የፈቀዱ የሃገሪቱ የጉዳዩ ተቆጣጣሪ ባለስልጣናትም በበጎ ፈቃደኞች ላይ ይሞከር መባሉን ቀጥሉበት ብለዋል፡፡
በጀርመኑ ባዮን ቴክ እና በግዙፉ የአሜሪካ መድሃኒት አምራች ተቋም ፒፋይዘር ለተዘጋጀው ክትባት (RNA) ፍቃድ የሰጠውም የፖል ኸርሊች የክትባትና የህክምና ተቋም ነው፡፡
ክትባቱ በመጀመሪያው ዙር ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 55 በሆኑ ጤነኛ 200 በጎፍቃደኞች ላይ ይሞከራል ተብሏል፡፡
በሁለተኛው ዙር ደግሞ በቫይረሱ ተጠቂዎች ላይ ጭምር ሰፋ ብሎ የሚሞከር ነው፡፡ መቼ ስለሚለው ግን የተባለ ነገር የለም፡፡ ክትባቱ በመላው ዓለም ላይ ተመሳሳይ ፍቃድን ካገኙ 4 የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች መካከል አንዱ ነው፡፡
ቀሪዎቹ 3 የክትባት መድኃኒቶች በካንሲኖ ባዮሎጂክስ እና በቤጂንግ ባዮቴክኖሎጂ ተቋም፣በአሜሪካው ኢኖቪዮ ፋርማሲውቲካልስ ፣ በሞደርና ቴራፒውቲክስ እና ዶ/ር ፋውቺ በሚመሩት በአሜሪካው ብሄራዊ የአለርጂ እና ተላላፊ በሽታዎች ተቋም የተዘጋጁ ናቸው፤ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው፡፡
ዩናይትድ ኪንግደምም ከዛሬ ሃሙስ ሚያዝያ 15/2012 ዓ.ም ጀምሮ ተመሳሳይ ሙከራን በበጎ ፈቃደኞች ላይ ማድረግ እንደምትጀምር ስለማስታወቋ ሲ.ጂቲ.ኤን ዘግቧል፡፡
እንደ ዓለም አቀፉ ድርጅት መረጃ ከሆነ ከ4ቱ በተጨማሪ 67 የኮሮና መድኃኒቶች በቅድመ ክሊኒካዊ ሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡
ይህም ነገር ነው ክትባቶቹ ምን ያህል ተስፋ ሊጣልባቸው የሚያስችሉ ናቸው? በምን ያህል ወራት ውስጥስ ይደርሳሉ? የሚለውን እንድንጠይቅ የሚያደርገን፡፡
በሙከራ ላይ ናቸው የሚባሉት የኮሮና ክትባቶች እውን ተስፋ ሰጪ ናቸውን?
እርግጥ ነው ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ቀን ማለትም እስከ ሚያዚያ 15/2012 ዓ.ም ድረስ በመላው ዓለም ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዬን በላይ ሰዎችን የያዘውን ወረርሽኝ ሊያስቆም የሚችል አንዳች ኃይል አልተገኘም፡፡ ከ186 ሺ በላይ ህይወትንም ነጥቋል፡፡ ይህ በሽታ አፋጣኝ ምላሽን የሚፈልግ ነው፡፡ የሟቾች ቁጥር ይበልጥ እንዳያሻቅብ ማድረግንም ይሻል፡፡ ለዚህም ርብርቡ ቀጥሏል፡፡
የተለያዩ መድኃኒቶችንና ክትባቶችን ለማዘጋጀት የሚደረገው ጥድፊያም የዚሁ ርብርብ አካል ነው፡፡ በተለይ አቅሙ ያላቸውና ያደጉ የሚባሉ ሃገራት የዓለም ጤና ድርጅትም ለጉዳዩ ቀዳሚ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ነው፡፡ ይህ መሆኑም ትልቅ ተስፋን የሚያጭር ነው፡፡
በቫይረሱ መነሻነት የምትጠቀሰው ቻይና ገና በማለዳው ነው ማብረሻ መድኃኒቶችን ማፈላለግ የጀመረችው፡፡ የተለያዩ የትምህርትና የምርምር ተቋማቶቿም ሌት ተቀን እየሰሩ ነው፡፡ ክትባቶችን ቀድሞ ለማዘጋጀት በሚደረገው እሽቅድምድም ተቋማቶቿ ከፊት ሆነው በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡
የወረርሽኙን ማብረሻ ቀድሞ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት ልክ ወረርሽኙን በቀላሉ መቆጣጠር እንደመቻል ያህል ልዩ የአቅምም የፖለቲካም ትርጉም የሚሰጠው ነው፡፡ ወረርሽኙን ለመቆጣጠርና ስርጭቱን ለመግታት እንዲሁም ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ለሌሎች ፈጥኖ ለመድረስ በሚደረገው ጥረት መመዘንም አለ፡፡ ለቀረበ ወዳጅነትና ቁርኝት መታጨቱም አይቀሬ ነው፡፡ ይህ ነገር ምናልባትም ዓለም አቀፋዊ ስርዓትንና የፖለቲካዊ አሰላለፍን መልክ የመቀየር አቅም አለው፡፡
ወረርሽኙን በመከላከል ረገድ “ደካማ” መስለው የተስተዋሉት ምዕራባውያን በዚህ ረገድ “ነጥብን ማስመዝገብ” ይፈልጋሉ፡፡ በድጋሚ “ደካማ” ሆኖ መታየትን የሚፈልጉ፣የሚፈቅዱም አይመስልም፡፡ ቀድሞ ለመገኘትም ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
ይህ ተስፋ ሊሰጥ የሚችል ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ተስፋው እስከ መቼ እውን ሊሆን ይችላል? የሚለው ተከትሎ መጠየቁ አይቀርም፡፡
መቼስ ይደርሳሉ?
መድኃኒቶች ሲዘጋጁ ፈውስን ያስገኙ ዘንድ ለገበያ ከመቅረባቸውና ተጠቃሚው ሰው ጋር ከመድረሳቸው በፊት የተለያዩ ሂደቶችን ያልፋሉ፡፡ ከአሁን ቀደም ከአል ዐይን አማርኛ ጋር የስልክ ቆይታ እንደነበራቸው በቅዱስ ጳውሎስ ሜዲካል ኮሌጅ የፋርማሲ ባለሙያና ፋርማኮሎጂስት (ረዳት ፕሮፌሰር) መንሱር ሻፊ ገለጻ፣ እነዚህ ሂደቶች የመድኃኒቶቹ ፈዋሽነትና ተያያዥ የጎንዮሽ ጉዳቶች በዝርዝር የሚጠናባቸው ናቸው፡፡
“የትኛውም መድኃኒት ቅድመ ክሊኒካዊ (Pre-clinical) ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት አጠቃላይ ሞለኪዩላዊ ባህሪው የጎንዮሽ ጉዳት ጭምር ይጠናል” የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ “የጎንዮሽ ጉዳት አለው የለውም የሚለው በእንስሳት ላይ ከተረጋገጠ በኋላ በተለያየ ደረጃ ሊጠቀሱ በሚችሉ ሂደቶች ውጤታማነቱ በበጎ ፈቃደኞች ከዚያም በታማሚዎች ላይ ይሞከራል” ሲሉ ያስቀምጣሉ፡፡
አንድን መድሃኒት ወደ ገበያ ለማስገባትና ጥቅም ላይ ለማዋል ዘለግ ያሉ ጊዜያት እንደሚያስፈልግም ይነገራል፡፡
የአሜሪካው ብሄራዊ የአለርጂ እና ተላላፊ በሽታዎች ተቋም መሪ ዶ/ር ፋውቺ “የኮሮና ቫይረስ መድኃኒቶችን ለማዘጋጀት ከ12 እስከ 18 ወራት ሊወስድ ይችላል” በሚል ስለመናገራቸውም ላይቭ ሳይንስን ጨምሮ የተለያዩ በጉዳዩ ላይ ሙያዊ ትንታኔዎችን የሚያሰፍሩ መጽሄቶች ከትበዋል፡፡
ይህ ደግሞ አሁን በሙከራ ላይ ናቸው፤ ሙከራው እንዲቀጥልም ፍቃድ ተሰጥቷቸዋል የተባለላቸው መድኃኒቶች ምናልባትም ከአመት በኋላ ግልጋሎት ላይ ሊውሉ እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው፡፡
ሆኖም በተባለው ጊዜ ስለመድረሳቸው መተማመን ይቻላል ወይ? ዘላቂነታቸውስ? እስከዚያው ድረስስ የምን ያህል ሰው ህይወት ሊያልፍ ይችላል? መልስ የሚሻው ጥያቄ ይህ ነው፡፡